የመንግስት ምሥረታና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ምሥረታና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን
ዛሬ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጰያ አዲስ ምእራፍ የተጀመረበት ዕለት ነው።
ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ 6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የምስረታና የመክፈቻ ጉባዔ ተካሂዷል።
በዚሁ የምስረታ ጉባዔ ላይ ምክር ቤቶቹ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በዋና እና ምክትል አፈ ጉባኤነት የሚያገለግሉትን የሥራ ኃላፊዎች ሰይሟል።
ምክር ቤቱ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ አብላጫ ወንበር ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የሚወክለውን ዕጩ ለምክር ቤቱ በማቅረብ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰይም ሲሆን በዚሁ መሠረት ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል።
የዶክተር ዓቢይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጥን አስመልክቶ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተው ዘግበዋል።
አሶሼትድ ፕሬስ፣ ቢቢሲ፣ ኤ.ኤፍ.ፒ፣ አልጀዚራ፣ ዋሸንግተን ፖስት፣ ብሉምበርግ፣ ቲ.አር.ቲ ዎርልድ፣ አናዶሉ፣ አል ዓረቢያ እንግሊዝኛ፣ ፍራንስ 24፣ ኤ.ቢ.ሲ ኒውስ፣ ዴይሊ ኔሽን፣ የጀርመን ድምጽ እና አፍሪካ ኒውስ ሽፋን ከሰጡት መገናኛ ብዙሃን መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ምስረታን እንዲሁም ዶክተር ዓቢይ አህመድ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ በድጋሚ ስለመመረጣቸው አስነብበዋል፡፡
ዶክተር ዓብይ አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ የተመረጡት እሳቸው የሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ በሰፊ ድምጽ ልዩነት አሸናፊ መሆን በመቻሉ እንደሆነም ዘግበዋል።
ባለፈው ሰኔ የተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከተካሄዱት ምርጫዎች በብዙ መመዘኛዎች የተሻለ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ስለመናገራቸውም አመልክተዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በቀጣይ የሥልጣን ዘመናቸው አገራዊ ሠላም እና አንድነት የማረጋገጥ እንዲሁም ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቃቸው አንስተዋል።
በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አገራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶች እና ድርድሮች እንዲካሄዱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ቀጣዩ የቤት ሥራ ሆኖ እንደሚጠበቅባቸውም በዘገባቸው አካተዋል።