ቀጥታ፡

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24/ 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫኪር ማያርዲት የኢትዮጵያን የጠቅላይ ሚኒስትር በዓለ ሲመት ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች አቀባባል አድርገውላቸዋል።

የ70 ዓመቱ ሳልቫኪር ማያርዲት ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2011 ራሷን የቻለች አገር ከሆነች ጀምሮ አገሪቷን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በነሐሴ 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት ላይ ለመታደም ዛሬ አዲስ አበባ የገቡ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ናቸው።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤ ዛሬ ከቀትር በፊት የተካሄደ ሲሆን፤ ዐቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም