ቀጥታ፡

ለተጀመሩ የለውጥ ሂደቶች ስኬት የዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ትልቅ እድል ነው

ሀረር፣ መስከረም 24/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለተጀመሩ የለውጥ ሂደቶች ስኬት የዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ትልቅ እድል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሾማቸውን ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር የሀረር ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

የክልሉ የመንግሥት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቢሮ ባዘጋጀው የቀጥታ ስርጭት መከታተያ መድረክ በርካታ ነዋሪዎች የመንግስት ምስረታ ሂደቱን ተከታትለውታል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ስንታየሁ ተሾመ፤ የዶክተር አብይ ድጋሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መሾም ኢትዮጵያ ለጀመረችው ልውጥ ስኬት የሚያመጣ ይሆናል ብለዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባሳለፍናቸው ጊዜያት ኢትዮጵያን ከመበታተን ያዳኑ ጠንካራ መሪና የለውጥ ሃይል ናቸው" ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰላምና ብልፅግና በማረጋገጥ ባለፉት ሶስት ዓመታት የጀመሯቸውን የልማት ስራዎች ያስቀጥላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የሀረሪ ክልል ነዋሪ ወይዘሮ ሙፍቱ አሊዩ፤ የዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ለኢትዮጵያዊያን መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙትን አቅድ እንዲያሳኩ ህዝቡ ድጋፍና እገዛውን አጠናክሮ በመቀጠል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥነት እንዲሁም የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን መፍታት የዶክተር አብይና መንግስታቸው ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገዋል ብለዋል።

የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ከግብ እንዲደርስ የዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የሀረር ከተማ ነዋሪ አቶ ቡሽራ አሊዩ ናቸው።

የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ማድረስና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ዋነኛ የትኩረት አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት ለውጥና የልማት ስራዎች በስኬት እንዲናወኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው ሊቆም ይገባልም ነው ያሉት።

ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ የፈፀሙ ሲሆን በመንግስት ምስረታው ስነ ስርአት ላይ ለመገኘት የተለያዩ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም