የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ አዲስ አበባ ገቡ
አዲሰ አበባ መስከረም 24/2014 /ኢዜአ/ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ምስረታ ስነ-ስርዓት ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፣ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አቀባባል አድርገውላቸዋል።
የ44 ዓመቱ ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ስራ የጀመሩት እ.አ.አ በሚያዚያ ወር 2021 ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የማዕድን ኩባንያ ጄካማይንስ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የኮንጎ ብሔራዊ የባቡር ኩባንያ ምክትል አስተዳደር በመሆን ሰርተዋል።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴ የምህንድስና ባለሙያ ናቸው።
የኢፌዴሪ መንግስት ምስረታውን ዛሬ እያካሄደ ሲሆን ዶክተር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
በዚሁ የመንግስት ምስረታ ሂደት መርሃ ግብር ላይ ለመገኘት ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።