"በአመፅና በጠመንጃ ትግልም ሆነ ንጹሀንን በማሸበር የሚገኝ ስልጣን ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር አይኖርም" - ኢዜአ አማርኛ
"በአመፅና በጠመንጃ ትግልም ሆነ ንጹሀንን በማሸበር የሚገኝ ስልጣን ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር አይኖርም"
አዲሰ አበባ መስከረም 24/2014 "በአመፅና በጠመንጃ ትግልም ሆነ ንጹሀንን በማሸበር የሚገኝ ስልጣን ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር አይኖርም" ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
የ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽ ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ ላይ ፕሬዚዳንቷ ባደረጉት ንግግር ባለፈው ዓመት ለዓመታት ዳር ድንበር ሲጠብቅ በኖረው የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን አስነዋሪ ጥቃት አስታውሰዋል።
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በንጹሃን ዜጎችና በመንግስታዊ ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችና የሽብር ተግባራትም "ከሕግና ከመርህ፣ ከሞራል፣ ከእሴቶቻችንና ባህላችን ያፈነገጡ ነበሩ" ሲሉም ተናግረዋል።
ይሁንና በአመጽና በጠመንጃ ትግልም ሆነ ንጹሃንን በማሸበር የሚገኝ ስልጣን ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር የማይኖር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
ስልጣን ሰጪውም ሆነ ነሺው "የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ የአገሪቷ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ በህጋዊ ምርጫ ብቻ በመሳተፍ አገራቸውን የሚያገለግሉበትን ሠላማዊ የፉክክር መንገድ ብቻ መምረጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሁሉም ከሕግ በታች በመሆኑ ማንኛውንም ጉዳይ ሕግ በሚፈቅደው አግባብ ብቻ ማከናወን እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕግን በማክበርና በማስከበር፣ መብትና ግዴታን በማገናዘብ ሊንቀሳቀስ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የሁሉም መጠለያ በሆነችው ኢትዮጵያ ከሕግም ሆነ ከአገር በላይ የሆነ ሃይል ሊኖር አይገባም ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ የሕግ የበላይነት በዘላቂነት እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲያዊነት እንዲገነባ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በአገሪቷ ለዓመታት የአገር ህልውናና የሕዝብ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንዲሁም ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ ሰንኮፎችን በብሔራዊ መግባባት መፍታት ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።
ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት ረዥም ጊዜ የሚሻ የለውጥ ሂደት በመሆኑ ይህ ብሔራዊ መግባባት ይሰፍን ዘንድ መላ ኢትዮጵያዊያን ያላሰለሰ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ይህንን ብሔራዊ መግባባት ለማምጣትም ሆደ ሰፊነት፣ መተማመን፣ መመካከር፣ ኅብረትና አንድነት፣ የውይይትና የክርክር ባህሎችን ማዳበር የሚያስፈልግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፍትህና ተጠያቂነት ማስፈን፣ የተጎዱትን መካስ ብሎም ማኅበራዊ ፍትህን ማስፈን የሚገባ መሆኑንም ተናግረዋል።