በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ማገልገል ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ ውሳኔ ተገዥነትንም ጭምር የሚያመለክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ማገልገል ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ ውሳኔ ተገዥነትንም ጭምር የሚያመለክት ነው
መሰከረም 24/2014 (ኢዜአ) በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ማገልገል ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ ውሳኔ ተገዥነትንም ጭምር እንደሚያመለክት መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮለኔል ጌትነት አዳነ፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 8 ቁጥር 2 ላይ "... ይህ ሕገ-መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ እንደሚል ገልጸው፣ “በመሆኑም የመከላከያ ሠራዊት ቃሉን ጠብቆ በከፈለው እልህ አስጨራሽ መሥዋዕትነት ሕዝብ ለመረጠው የመንግሥት ምሥረታ በቅቷል” ብለዋል።
"በዚህም በጓዶቻችን መሥዋዕትነት ለተመሠረተው መንግሥት መብቃታችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለንን ታማኝነት ያረጋገጥንበት ስለሆነ ሉዓላዊነታችንን ጠብቀን ከዚህ ስለደረስን ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል" ነው ያሉት።
"ሥልጣን በምርጫ ብቻ የሚያዝ እንጂ በማንኛውም አቋራጭ መንገድ የሚፈፀም አለመሆኑን ሕገ-መንግሥቱ ደንግጓል፤ ሠራዊቱም ለዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ እውናዊነት ታሪክ የሚያወሳው ዋጋ ከፍሏል" ብለዋል።
ኮለኔል ጌትነት፣ “የመከላከያ ሠራዊት ቃሉን ጠብቆ ለሕግ የበላይነት ሲተጋ የመጨረሻ ምሽግ መሆኑን ያወቁ ሀገር አፍራሽ ኃይሎች ከውጭ እና ከውስጥ ያላቸውን አማራጮች ሁሉ ተጠቅመው ገጥመውናል።
ይሁን እንጂ ደማችን ጎርፍ ሆኖ ወስዷቸዋል፤ አጥንታችን እሾክ ሆኖ ወግቷቸዋል፤ ያፈረሱት ቃል እንጂ ሀገር እንደሌለ አሳይተናቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ወደፊትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመረጠው መንግሥት በመታዘዝ እና የኢትዮጵያን አንድነት ዛሬም እንደትናንቱ በትግላችን የታፈረች እና የተከበረች ሀገር ለመጭው ትውልድ እንደምናስረክብ እርግጠኞች ነን በማለት መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።