የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23/2014(ኢዜአ) የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ምስረታ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ገቡ።
ፕሬዚዳንት ቡሐሪን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና ሌሎች ከፍትኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ቀደም ሲል በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በጤና፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በአየር አገልግሎት እና ግብርናን ጨምሮ ከ13 በላይ ሴክተሮች በጋራ ለመስራት የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ከከፍተኛ የነዳጅ አምራች አገራት መካከል የምትጠቀሰው ናይጄሪያ በአመት በአማካይ ከ6 እስከ 8 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት የምታስመዘግብ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ በ1953 ዓ.ም በሌጎስ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን ናይጄሪያ ደግሞ በ1955 ዓ.ም ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ።