ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማሻገር በጋራ እንሰራለን

ሀዋሳ፤ መስከረም 23/2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ አሁን የተደቀነባትን ፈተና ተሻግራ ከፍ እንድትል በትብብር የሚሰሩ መሆኑን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ገለጹ ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ችግሮች በመውጣት ሁለንተናዊ እድገት እንዲመጣ በሚደረገው ጥረት በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ተወካይ አቶ መንግስቱ ቢፍቱ ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተለየ ምልኩ አንፃራዊ ዴሞክራሲዊነት የሰፈነበትና ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን አስታውሰዋል።

''ችግሮች ቢኖሩም ምርጫውን ተጋግዘን በመስራት ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አድርገናል'' ያሉት አቶ መንግስቱ ኢትዮጵያ የተደቀነባትን ፈተና ተሻግራ እኩልነትና ሁለንተናዊ እድገት እንዲመጣ ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከአማሮ ልዩ ወረዳ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ተወካይ ወ/ሮ ታደለች ታሪኩ በበኩላቸው ከምንም በላይ ለአገር ቅድሚያ ሰጥተው እእንደሚሰሩ ተናግረዋል።

መንግስት በላይኛው መዋቅር ያለውን የለውጥ ጅማሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ማውረድ እንደሚጠበቅበት ገልጸው፤ ይህንን ከዳር ለማድረስ ተባብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

''ወክለነው የመጣነው የአማሮ ህዝብ ከፍተኛ የሠላም እጦት፣የልማትና መልካም አስተዳደር ችግር ያለበት ነው'' ያሉት ተመራጯ እነዚህን ችግሮች የክልሉ መንግስት እንዲፈታ በምክር ቤቱ ሠላማዊ የሀሳብ ትግል እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

ከጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ወክለው የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ''ቅድሚያ ለአገር ግንባታ ሰጥተን በይደር የቆዩም ሆኑ በአዲስ መልክ የሚነሱ የህዝብ ጥቄዎች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ለማድረግ እንሰራለን'' ብለዋል።

''በምርጫ ወቅት የነበሩ ፈተናዎችን ያለፍነው ተባብረን ስለሰራን ነው'' ያሉት አቶ ታረቀኝ በጋራ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ከየትኛውም አካል ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተጋግዘው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በምርጫ ወቅት የነበረው የመሪና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥምረት በቀጣይ በሌሎች የልማት ስራዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ትናንት ባካሄደው የመንግስት ምስረታ ጉባኤ ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የተካተቱበት የአስፈጻሚ አካላትን ሹመት ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም