የቡርጂ ወረዳ ነዋሪዎች የለውጥ ሂደቱን በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ

69
ሃዋሳ ነሃሴ 10/2010 በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የቡርጂ ወረዳ ነዋሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ዛሬ ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ ገለጹ፡፡ የሰልፉ አስተባባሪ አቶ ደጉዬ ሻኖ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍንና የመደመር፣ የፍቅርና የይቅርታ ሀገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያከናወኑ ያሉት ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የወረዳው ህዝብም ከጎረቤትና ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ለዘመናት የቆየውን በጋራና በፍቅር የመኖር ልምድ አጠናክሮ በመቀጠል ለአገራዊ የለውጡ ስኬታማነት የበኩሉን እንደሚወጣ እምነታቸውን ገልፀዋል ፡፡ ''ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጉጂ ኦሮሞ ጋር ያለንን የአብሮነት ስሜት ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እያከናወኑ ያሉት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት የቡርጂ ብሔር ተወላጆች ላይ መፈናቀል አስከትሏል'' ብለዋል፡፡ ይህን ችግር በተጀመረው የመደመርና የይቅርታ መርህ መሰረት እንዲፈታ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የወረዳው 26 ቀበሌ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የተዘጉ ከሶያማ - ቡሌ ሆራ እንዲሁም ከሶያማ-ዲላ መንገድ እንዲከፈትና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም