ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞች ችግር አዲስ በሚመሰረተው መንግስት የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ እንሻለን

አዳማ ፣ መስከረም 23/2014(ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ከቀደመው የተሻለ ትኩረት እንዲያገኝ እንደሚሹ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገለጹ።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ አዲሱ መንግሥት የአካል ጉዳተኞች መብት ማክበር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ያስተካክላል ብለን እንጠብቃለን ብሏል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደገለጹት አካል ጉዳተኞች አዲሱ መንግሥት በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ መመዘኛ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንዲያደርጉ ይፈልጋሉ።

አካል ጉዳተኞች የመሪነት ሚና እንዲኖራቸውና በአገር ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻል ከአዲሱ መንግስት የምንጠብቀው ተግባር ነው ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች መስራት የሚችሉ፣ዕውቀትና አቅም ያላቸው መሆኑን አምኖ የሚቀበልና በትክክል የሚያሳትፍ መንግሥት መሆን አለበት ያሉት አቶ ዓባይነህ፤ የአካል ጉዳተኞች ሕግ እንዲወጣ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

በፌዴራልና በክልሎች እየተቋቋሙ ባሉት መንግሥታት በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሆነው 99 ወንበሮች ከተወዳደሩት አካል ጉዳተኞች 66ቱ ማሸነፋቸውን ገልጸዋል።

በምርጫው በንቃት መሳተፋቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ መልክ ሲደራጅ አካል ጉዳተኞች የሚመለከቱ ግብዓቶች እንዲካተቱ በማድረግ ሚና ከመጫወት ባሻገር፤ ሕጉ ተፈፃሚ እንዲሆን ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

አዲሱ መንግሥት የአካል ጉዳተኞች መብትን በማክበርና ማስከበር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ያስተካክላል ብለን እንጠብቃለን ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ እርግብ ገብረሃዋርያ ናቸው።

በተለይ አካል ጉዳተኞችን በአመራርና በፖለቲካ ተሳትፎ ማብቃት፣ የዘርፍን ማህበራት መደገፍና ማጠናከር ከአዲሱ መንግስት የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም ያሉት ኮሚሽነሯ፣ መንግሥት በቀጣይነት በዘርፉ በሚያከናውናቸው ተግባራት ችግሩን መፍታት አለበት ብለዋል።

በዚህም የአካል ጉዳተኞችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይረጋገጣል የሚል ተስፋና እምነት ከአዲሱ መንግሥት እንደሚጠብቁ ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም