በእርዳታ ሽፋን የተወጠነ ሀገር የማፍረስ ሴራ - ኢዜአ አማርኛ
በእርዳታ ሽፋን የተወጠነ ሀገር የማፍረስ ሴራ
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የወጠነው የዓመታት ሴራ ገሀድ የወጣው ጥቅምት 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም ነበር።
የሽብር ቡድኑ ይህን እርምጃ የወሰደው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ዓይነት ብሂል የሀገርን ሉአላዊነት አሳልፎ ለመስጠት አልሞ የነበረ ቢሆንም በጀግናው መከላከያ ሠራዊት ሴራው ሊከሽፍ ችሏል።
የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉና የአሸባሪውን ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራ የሚደግፉ አንዳንድ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቡድኑ የከፈተውን በር በመጠቀም ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል “እርዳታ እናሰራጫለን” በሚል ሽፋን የፖለቲካ ሸፍጥ ሲሰሩ ቆይተዋል።
እነዚህ በአንዳንድ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የውጭ አገር ዜጎች ለአሸባሪው ቡድን በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ግለሰቦቹ ለሽብር ቡድኑ የሳተላይት ስልኮችን ጨምሮ ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ጀምሮ በሱዳን በኩል ኮሪደር እንዲከፈት በመንግስት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ያላደረጉት ትግል አልነበረም።
ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያን ስምና ዝና የሚያጠለሹ በርካታ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችን ከፍተው ሲሰሩ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህ የዓለም አቀፍ ድርጅት ሰራተኞች ከመርህ ያፈነገጠ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን በማመልከት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በማስረጃ አስደግፎ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል።
ይሁን እንጂ ከድርጊታቸው ከመታረም ይልቅ ከአሸባሪው ቡድን ሀገር የማፈረስ ሴራ ጋር አብረው መስራታቸውን አላቆሙም።
ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር መገባደጃ መንግስት ሶስት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከተቋቋሙለት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ መገኘታቸውን በመጥቀስ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ለሶስት ወራት እንዲታገዱ አድርጓል።
እነዚህ ድርጅቶች MSF HOLLAND፣ NORWEGIAN REFUGEE COUNCIL እና AL MAKTOUME FOUNDATION የተባሉ ሲሆኑ ከተቋቋሙበት አላማ ውጭ የሀገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ለድርጅቶቹ ሃላፊዎች ቢገለጽም ሊያስተካክሉ አለመቻላቸውን በወቅቱ መንግስት አሳውቋል።
አሁንም አንዳንድ የውጭ ሀገር ሰራተኞች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሚተዳደርባቸው የዓለም አቀፍ መርሆዎች በተቃረነ መልኩ በሉአላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገብተው ትእዛዝ እስከመስጠት የደረሰ ህገ ወጥ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል።
እነዚህ ሰራተኞች አሸባሪው ቡድን በአማራና በአፋር ክልል የፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ አንድም ነገር ሳይተነፍሱ ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ የሚሰራጭበትን ተጨማሪ ኮሪደር እንዲከፈት ሲወተውቱ ሰንብተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሱዳን ቀጥታ እርዳታ ለማስገባት በሚል ተጨማሪ መተላለፊያ ኮሪደር እንዲከፈት የሚቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መንግስት በተደጋጋሚ አሳስቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሰብዓዊ ደጋፍ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ትግራይ ገብተው ሳይመለሱ የቀሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች በአሸባሪው ህወሃት ቁጥጥር ስር ውለው ለወታደራዊ ተግባር እየተጠቀመባቸው ስለመሆኑ በቂ መረጃ እያለው የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሲያወግዝ አልታየም።
በሀገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም አሸባሪው ህወሓትን ከመንካት ይልቅ መንግስት ላይ ማነጣጠር የእለት ተለት ተግባራቸው ሆኗል።
የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በአፋር እና በአማራ ክልሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው እርዳታ ፈላጊ ቢሆኑም ለድርጅቶቹ ደንታም አልሰጣቸውም።
ይልቁንም ትኩረታቸው ሀገር ለማፍረስ የወጠኑትን ሴራ በሚያሳኩበት መንገድ ላይ አድርገዋል።
መንግስት ለዜጎች ካለው ቀናኢ አስተሳሰብ የተነሳ በትግራይ ክልል የእርዳታ ስርጭት እንዳይስተጓጎል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን ከመወሰን ጀምሮ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች ወደ ክልሉ የሚገቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ መንግስት ለሚያደርገው ጥረት እውቅና ከመስጠት ይልቅ “ለትግራይ ህዝብ እርዳታ እንዳይደርስ በእጅ አዙር እቀባ አድርጓል” የሚሉ ፕሮፖጋንዳዎችን ማስተጋባት ተያይዘዋል።
መንግስት ከሰሞኑ ከብዙ ትዕግስት በኋላ ህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ሰጪ ሰራተኞች በ72 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
እነዚህ ሰባት የተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች ከሀገር ለመባረር ያበቃቸው ከሙያቸው ሥነ ምግባር ውጭ እርዳታን አሽብር ቡድኑ እንዲደርስ በማድረግ፣ የተለያዩ መገናኛ መሳሪያዎች ቡድኑ እንዲጠቀምባቸው በማስተላለፍ፣ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማሰራጨትና ሰብአዊ እርዳታን ለፖለቲካ ዓላማ እንዲውል በማድረጋቸው መሆኑን መንግስት ይፋ አድርጓል።
ይህ እርምጃ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ከሚያስጨንቀው ከአንድ ሉዓላዊ ሀገር መንግስት የሚጠበቅ ትክክለኛ እና ተገቢነት ያለው ስለመሆኑ በርካታ ምሁራን ይናገራሉ።
ምሁራኑ እንደሚገልጹት የትኛውም የውጭ አገር መንግሥት ይሁን ዓለም አቀፍ ድርጅት አንድን ተግባር ለማከናወን ሲገባ የሀገሪቷን ሕግና ደንብ አክብሮ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
ከዚህ ውጪ በየትኛውም ወንጀል ተሳታፊ ሆኖ ከተገኘ የየትኛውም ሀገር መንግሥት ድርጊቱን በዝምታ የሚያይበት የሕግም ሆነ የሞራል መሠረት አይኖረውም ባይ ናቸው ምሁራኑ።
ብዙዎች እንደሚናገሩት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋሙ ድርጅቶች የራሳቸው የሆነ ገለልተኝነት፣ ሚዛናዊነት፣ ሰብአዊነትና ነፃነትን መሠረት ያደረጉ መርሆዎችና ሕግጋቶች አሏቸው።
ለሰብአዊነት ተግባር የተሰማሩ ሠራተኞች ከተቋቋሙለት መርህ ውጪ የአንድን ሀገር ሉአላዊነትና ሕግ በሚጥስ መልኩ ሲሰሩ በመገኘታቸው የሚወሰድ እርምጃ አግባብነት ያለው ነው በማለት ይገልጻሉ።
ከዚህ አኳያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ይናገራሉ።
የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎ ከየተባበሩት መንግስት ድርጅትም ይሁን አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያሰሙት የተቃውሞ ድምጽ ግርምትን የሚፈጥር ሆኗል።
ብዙዎች እንደሚናገሩት ሀገራቱም ይሁን ድርጅቶቹ በእርግጥ ለፍትሐዊነት የሚቆሙ ከሆነ አሸባሪው ህወሓት በአፋር እና በአማራ ክልል ለሚያደርሰው ጥፋት ተጠያቂ ያደርጉ ነበር። በክልሎቹ ንጹሃንን በገፍ ሲጨፈጭፍ፣ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት ሲገድል፣ የዜጎችን ሀብት ንብረት ሲዘርፍና የመንግስት ተቋማትን ሲያወድሙ ሊያወግዙ ይገባ ነበር።
ለእውነት የቆሙና ትክክለኛ የሞራል ልዕልና ቢኖራቸው ሊያስደነግጣቸው የሚገባው የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው ትግራይ የቀሩ መኪኖች የመቅረት ጉዳይ በሆነ ነበር።
የድርጅቶቹ ተቃውሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ የ1961 የቪየና ኮንቬንሽን አንቀጽ 9 ላይ ካለው መርህ ጋር የሚቃረን ነው።
ስምምነቱ ሀገራት ማንኛውም የዲፕሎማሲ ሠራተኛ አባል በማንኛውም ጊዜ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሳይሰጥ የማስወጣት መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል።
ይህ ሆኖ እያለ አሁን ላይ በተወሰደው እርምጃ ጩኸት ማሰማታቸው ለጥቅማቸው እንጂ ለሰብአዊነት የቆሙ እንዳልሆኑ አሳይቷል።
አሜሪካ ሉአላዊነቴን ተዳፍረዋል ያለቻቸውን የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች የሆኑ የሩሲያና የቻይና ሠራተኞችን በ24 ሰዓታት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ስታደርግ ተቃውሞ ስለምን አልገጠማትም? በማለት የህግ ባለሙያዎች ይሞግታሉ።
እናም ኢትዮጵያ ልክ እንደ አሜሪካ እነዚህን አካላት የማስወጣት ተመሳሳይ የሆነ የሕግ መብት እንዳላት ያስረዳሉ።
መንግስት ከመርህና ከህግ ባፈነገጠ መልኩ እርዳታን ሽፋን በማድረግ ለአሸባሪው ቡድን ሲሰሩና በሀገር ህልውና ላይ አደጋ በሚፈጥሩ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ሲወሰድ ጫጫታ መፍጠርና ጫና ለማሳደር መሞከር በውስጡ ሀገር የማፍረስ ሴራ ያዘለ ስለመሆኑ ነጋሪ አያስፈልገውም።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጽም፣ በኋላም “ሂሳብ አወራርዳለሁ” በሚል ወደ አማራና አፋር ክልሎች ጥቃት ሲሰነዝር፣ በርካታ ንጹሀን ሲጨፈጨፉ ዝምታን መርጦ በህገ ወጥ ተግባር እርምጃ ሲወሰድ መቃወም ከዓለም አቀፍ መርህ ያፈነገጠና በሴራ የተለወሰ ተግባር ነው።