ቀጥታ፡

በዘንዘልማ መጠለያና ከመጠለያ ውጭ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከነገ ጀምሮ ቋሚ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል

ባህር ዳር ፤ መስከረም 22/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በዘንዘልማ መጠለያና ከመጠለያው ውጭ ከዘመድ ጋርና ቤት ተከራይተው ለሚገኙ ዜጎች ከነገ ጀምሮ ቋሚ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ በሚገኘው መጠለያ ማዕከል ለተጠለሉ ወገኖች መንግስት የዕለት ምግብ ፣ የቁሳቁስ እና አልባሳት ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ እና የካቢኔ አባላት ዘንዘልማ በሚገኘው የመጠለያ ማዕከል ከዋግህምራ ዞን የመጡ ተፈናቃዮችን ዛሬ በመጠየቅ አበረታትተዋል።

የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የሎጂስቲክስ ጊዜያዊ አስተባባሪ ወይዘሮ ዝና ጌታቸው በወቅቱ እንዳሉት፤ ዘንዘልማ በሚገኘው መጠለያ እስካሁን ድረስ ከመንግስት የተደረገ ድጋፍ የለም።

ለተፈናቃዮች የዕለት ምግብ እያቀረበ ያለው የባህር ዳር ከተማና አካባቢው ወጣቶችን ጨምሮ ሌላውም ህብረተሰብ እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች በጎ ፈቃደኛ ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም ለባህር ዳር ከተማና ለአካባቢው ህዝብ ነዋሪዎች በተፈናቀሉ ወገኖች ስም ምስጋና ያቀረቡት ወይዘሮ ዝና፣ በመጠለያው የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ህፃናትና ሌሎች አቅመ ደካሞች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በቋሚነት የዕለት ምግብ ፣ለመስሪያ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ፣ አልባሳትና ፍራሽን ጨምሮ ሌሎችንም ድጋፎች መንግስት እንዲያቀርብላቸ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ሰጭ ዳይሬክተር አቶ ጀምበሩ ደሴ በበኩላቸው በአሸባሪው ህወሓት ወረራ በርካታ ቁጥር ያለው የክልሉ ህዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባህር ዳር፣ እብናትና ሌሎች አካባቢዎች በተቋቋሙ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለተጠለሉ ከ500 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች የተሟላም ባይሆን ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በአብዛኛው እየተሰጠ ያለው የስንዴ ዱቄት መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ዘይትን ጨምሮ ለእናቶችና ለህፃናት የሚሆን የአልሚ ምግብና የጥራጥሬ እህል እጥረት መኖሩን ጠቁመዋል።

በተለይም የአልባሳት፣ የማብሰያ ቁሳቁስ፣ የብርድ ልብስ፣ የፍራሽና ምንጣፍ ችግርን ጠቅሰዋል።

በዘንዘልማ መጠለያና ከመጠለያው ውጭ ከዘመድ ጋርና ቤት ተከራይተው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከነገ ጀምሮ ቋሚ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ፤ በርካታ ወገኖች በአሸባሪው ቡድን ጥቃት ተፈናቅለው በየአካባቢው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ለይቶ ለመፍታት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ህብረተሰቡና ሌሎች ተቋማትም የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባህር ዳርና አካባቢው ህዝብ በመጠለያ ለሚገኙ ወገኖች እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም ይህን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አመልክተዋል።

"ተፈናቃዩ ነገ ነፃ በመውጣት ወደ ሞቀ ቤቴና ወደ ስራዬ እመለሳለሁ፣ የሰላም አየር እተነፍሳለሁ የሚል ተስፋና ወኔን በውስጡ መሰነቅ ይኖርበታል ሲሉም" ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ በተለይ ወጣቶች አሸባሪውን የህወሓት ኃይል ለመፋለምና ከክልሉ ጠራርጎ ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት የፀጥታ ኃይሉ የትግል አካል ሆነው እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዘንዘልማ መጠለያ ከሦስት ልጆቻቸውና ባለቤታቸው ጋር የሚኖሩት ወይዘሮ የዋግነሽ መንግስቱ፤ የባህር ዳር ህዝብ ልጆቻቸው እንዳይራቡ እስካሁን እያደረገ ላለው የዕለት ምግብ ድጋፍ አመስግነዋል።

መንግስት አሸባሪውንና ወራሪውን ኃይል ከክልሉ ጠራርጎ በማስወጣት ወደቄያቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወታቸውን የሚኖሩበትን ሁኔታ እንዲያመቻች እንደሚፈልጉም አንስተዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩና የካቢኔ አባላት የባህር ዳር ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ የሥራ እንቅስቃሴንም እንደጎበኙ ቀደም ብሎ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም