የዘንድሮው ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል አከባበር የህዝቡ ሠላም ፈላጊነት ያሸነፈበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል አከባበር የህዝቡ ሠላም ፈላጊነት ያሸነፈበት ነው

ቢሾፍቱ ፤ መስከረም 22/2014 (ኢዜአ) "የዘንድሮ ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል አከባበር የህዝቡ ሠላም ፈላጊነት አሸናፊ የሆነበት ነው" ሲሉ የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከበደ ዴሲሳ አስታወቁ።
የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደርና አባ ገዳዎች ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው አቶ ከበደ ዴሲሳ እንዳሉት፤ የዘንድሮ የሆራ ፊንፊኔ እሬቻ በዓል በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት ያለምንም ችግር በሠላም ተከብሮ ህዝቡ ወደ ሚቀጥለው ቢሾፍቱ ኢሬቻ እየተመመ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ህዝብም የኢሬቻ አከባሪ እንግዶችን ውሃና ምግብ እየሰጠ በመቀበልና በማስተናገድ ላደረገው የተለመደ ጨዋነቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
በሆራ ፊንፊኔ የተከበረው የኢሬቻ በዓል የህዝቡ ሠላም ፈላጊነት አሸናፊ ሆኖ ያሳየበት ነው ሲሉ አቶ ከበደ አስታውቀዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አለምፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ከተማችን እንግዶቿን በሠላም ተቀብላ ለመሸኘት ዝግጅቷን አጠናቃለች ብለዋል።
አባ ገዳዎችም፤ እንግዶቻችን ወደ ውቢቷ ቢሾፍቱ ኑ ባህላችሁን አክብሩ በሠላም ወደየቤታችሁም ተመለሱ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።