አንድነትንና መረዳዳትን ለቀጣይ ትውልድ የማቆየት ሃላፊነት አለብን- ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
አንድነትንና መረዳዳትን ለቀጣይ ትውልድ የማቆየት ሃላፊነት አለብን- ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል
ጅማ፤ መስከረም 22/ 2014 (ኢዜአ) አንድነትን፣መተሳሰብንና መረዳዳትን ለቀጣይ ትውልድ የማቆየት ሃላፊነት አለብን ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ተናገሩ።
ሚኒስቴሩ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በብሔራዊ የበጎ ፍቃድ አገልገሎት ያሰለጠናቸውን ከ5ሺህ 600 በላይ ወጣቶች ዛሬ አስመረቋል።
በጅማ ከተማ በተካሄደው የምረቃ ሥርዓት ላይ የተገኙት ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር ፤ የበጎ ፈቃድ ሰልጣኝ ወጣቶች መርዳትን፣መተሳሰብን፣ ፍቅርና አንድነትን በተግባር ሲማሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
አንዱ የሌላውን ቋንቋ በመማር መልካም ተሞክሮ አግኝተዋል ብለዋል።
"መስጠት የፍቅር መገለጫ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ወጣቶቹ ካላቸው ትንሽ ነገር ለሌላው በማካፈል የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ በጎነትን በተግባር ሲለማመዱ እንደነበር አውስተዋል።
ፕሮግራሙ በዚህ ከቀጠለ በሀገሪቱን መልካም ገጽታ መመለስ እንደሚቻል የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈርያት፤ ይህም አንዱ የሌላውን ቋንቋ የሚማርበትና ባህሉን የራሱ በማድረግ አንድነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።
በቀጣይም አንድነትን፣መተሳሰብንና መረዳዳትን ለቀጣይ ትውልድ የማቆየት ሃላፊነት አለብን ብለዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ በመቀበልና በብቃት ለሁለተኛ ዙር ለምረቃ አብቅተናል ብለዋል።
ሀገራችን ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለሀገር በጎ ገጽታና ለብሔራዊ መግባባት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ተመራቂዎች ሰናይ ምግባራቸውን ይቀጥሉ ዘንድ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተመራቂዎቹ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተውጣጥተው ባለፉት 45 ቀናት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሰለጠኑና መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ስልጠና አስተባባሪ ወይዘሮ ትዕግስት ኃይለማሪያም ናቸው።
ወጣቶቹ ከከፍተኛው የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ሲሆን፤ በሀገር ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ በስራ እድል ፈጠራና ከወጣቱ ለሀገር እድገት ተጠባቂ ተግባራትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ነው የሰለጠኑት።
ተመራቂ ወጣቶቹ ከአካባቢያቸው ውጭ በተመደቡበት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሄደው ህብረተሰባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከወጣቶቹ መካከል ነኢማ ነጃ ፤ በስልጠናው ለሰዎች መልካም ማድረግ የሚሰጠውን ውስጣዊ ሀሴት ተረድቻለው ብላለች።
በቻልነው ሁሉ እገዛ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን እናግዛለን ነው ያለችው።
ሌላው ተመራቂ በላይ ተሰማ በበኩሉ፤ በርካታ በጎ ተግባራትን በማከናወን ሲማሩ እንደቆዩ በመግለጽ ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል።
"መልካምነትና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባለን ነገር ማገልገልና ካለን ነገር ቀንሰን ለሌለው መስጠት ነው" ብሏል።
ሰልጣኞቹ በቀጣይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመድበው የበጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።