ቀጥታ፡

በሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የተንጸባረቀው ኢትዮጵያዊ ፍቅርና ወንድማማችነት አገር ለመገንባት ታላቅ እሴት ነው

አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 22/2014 በሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የተንጸባረቀው ኢትዮጵያዊ ፍቅርና ወንድማማችነት አገርን ለመገንባት ታላቅ እሴት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ የበዓሉን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢሬቻ በዓል በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ፣ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ መከባበርና ወንድማማችነት በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የበዓሉ ታዳሚዎች፣ ወጣቶች፣ የጸጥታ አካላትና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

ከንቲባዋ የህዝብ በዓላትን፣ የብሔሮች ብሔረሰቦች ወጎችና ልማዶች በተለየ ሁኔታ ማክበር የህዝብን አንድነትና አብሮነት ለማጠንከር የሚያስችል እሴት መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህ ቀደም ግን "አንዱ የአንዱን ያጠፋል" የሚል የተሳሳተ ትርክት ሲነገር መኖሩን አስታውሰዋል።

የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ያሳየን "የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ አብሮነት የህዝቦቿ በጋራ መሆን ነው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ ታዳሚዎች ያሳዩት ፍቅር፣ ወንድማማችነትና እንክብካቤ አገርን ለመገንባት ትልቅ እሴት መሆኑንም ተናግረዋል።

በከተማዋ የኢሬቻ በዓል መከበሩ ወንድማማችነት፣ ሰላምን መስበክና ፈጣሪን ማመስገን ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጭምር የጠነከረበት መሆኑን ገልጸው፤ የዚህ ዓይነቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪው አሸባሪው ሸኔ ኢሬቻ ወግና እሴቱን ጠብቆ እንዳይከበር ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች ህዝቡ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ ያደረገውን አስተዋጽኦ በሆራ አርሰዴም እንዲደግመው ጥሪ አቅርበዋል።

ኢሬቻ ከክረምቱ ጭጋግና ጉም ጫና በመውጣት ወደ ብርሃን ዘመን ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት የሠላምና የአብሮነት በዓል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም