የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል የምናደርገውን ድጋፍ አናቋርጥም - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል የምናደርገውን ድጋፍ አናቋርጥም
መስከረም 22/2014(ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደማያቋርጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች አረጋገጡ።
አጠቃላይ ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ የመጀመሪያ ዙር ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ቢያልፍም ፍሬውን ሊያፈራ ጥቂት ወራት ብቻ ቀርቶታል።
ለዚህ ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት በሚችለው አቅም አሻራውን ያላሳረፈ ኢትዮጵያዊ ማግኘትም ከባድ ነው።
ኢትዮጵያዊያን የአንድነታቸው፣ የጥንካሬያቸውና የህብረታቸው ማሳያ መሆኑን አምነው፤ በእውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የሚያረጋግጡት።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን አልምታ እንዳትጠቀም የፋይናንስ ድጋፍ ከመከልከል ጀምሮ የግድቡ ግንባታ እንዲጓተት የተለያዩ ሴራዎች እንደነበሩ በሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ላይ የታደሙ አስተያየት ሰጪዎች ያወሳሉ።
ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት ለግድቡ ግንባታ በሰጠው ልዩ ትኩረት ክፍተቱ ተስተካክሎ ግንባታው እንዲፋጠን ማድረጉ የሚመሰገን መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ግድቡ ሃይል አመንጭቶ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ እንዲለመልም ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደማያቋርጡ አስተያየት ሰጪዎቹ አረጋግጠዋል።
ወይዘሮ ጸሃይ ገመቹ'' ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ነው ለአሁን እንቸገር የወደፊቱን አይተን አሁን መቸገር ይሻላል'
አቶ ሃይሉ ለማ በበኩላቸው ባለን አቅም በእውቀትም 8100 ላይ አጭር መልዕክት ለህዳሴ ግድብ መክፈል አለብን ብለዋል ።
''ህዳሴ ግድብ እንግዲህ ዛሬ እዚህ ደርሰን እንደምናየው አይደለም በጣም ብዙ ቻሌንጆች እንደነበሩ እናውቃለን የውጭ ምንዛሬ እንኳን እንዳናገኝ በጣም ብዙ ትልቅ ቻሌንጅ ሲፈጠርበት እንደነበረ ከውስጥ ከውጭ ከግብጽ ጋርም ተያይዞ የህዳሴ ግድባችን የህልውና ጉዳይ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት አሰባስቦ የገነባውን ሊጠብቅ ይገባል በቀጣይ ለበርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠርበት ነው የህዳሴ ግድብ እነዚህን ነገሮች ተጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል በፈቀደ አቅም።'' ያሉት ደግሞ አቶ መርጋ ለገሰ ናቸው ።
ባለፉት አስር ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ከህዝብ ማሰባሰብ መቻሉን ከግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።