የበዓላት በሠላም መከበር ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ለሚሹ ሃይሎች መልዕክት አለው - ኢዜአ አማርኛ
የበዓላት በሠላም መከበር ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ለሚሹ ሃይሎች መልዕክት አለው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2014(ኢዜአ) የአደባባይ በዓላት በሠላም መከበራቸው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ለሚፈልጉ ሃይሎች ትልቅ መልዕክት እንዳለው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።
ታዳሚዎቹ ኢትዮጵያን ለመበታተን ከውስጥና ከውጭ የሚደረጉ ጫናዎች በሕዝቦቿ የተባበረ ክንድ እንደሚከሽፉም ነው የተናገሩት።
የሆራ ፊንፊኔን በዓል ከኦሮሞ ባሻገር የተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦችም በአንድነት አክብረውታል።
ከኢዜአ ጋር ቆይ ያደረጉ የበዓሉ ታዳሚዎች ኢሬቻ የሠላም፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የፍቅር በዓል መሆኑን ዓለም ሊረዳ ይገባል ይላሉ።
በተለይ ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ተጠቅመው የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የሚፍጨረጨሩ ሃይሎች የኢትዮጵያዊያንን የአንድነት ስነ-ልቦና ያልተረዱ ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት በሠላማዊ መንገድ የመከበራቸው ምስጢርም የሕዝቡን ሠላም ወዳድነትና መቻቻል ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአደባባይ በዓላት በሠላም ተከብረው መጠናቀቃቸው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ለሚፈልጉ አካላት ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
አቶ አዲና አህመድና የሀላባው አቶ ደስታ ረኪሶ የሲዳማእንዳሉትወደ ኢትዮጵያ እጃቸውን የሚያስገቡ ሃይላትና መንግስታት እጃቸውን እንዲያወጡ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ለመመከት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስትም ሠላምና መረጋጋት ማስፈን ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው ነገር ግን ሠላምን ከመንግስት ብቻ መጠበቅ ተገቢ አለመሆኑንም አንስተዋል።
በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ መመከት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ አመለክተዋል።
አቶ አዲና አህመድ-ከሀላባ "የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፈው ጊዜ በምርጫ ላይ እንዳሳየው አሁን አዲስ በሚመሰረተው መንግስትም ጎን ሆኖ ከውጭም ይሁን ከውስጥ የሚደረጉ የትኛውንም ተጽዕኖዎች ተቋቁሞ በሠላም ኢትዮጵያን ማሻገር፤ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እንድትቀጥል የሁሉም የኢትዮጵያ ዜጋ ሃላፊነት መሆን አለበት።"
ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ፈተናዎችን እንዲሁም ስኬቶችን ማስተናገዷ ይታወቃል።
ከስኬቶቹ መካከል 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆና ያለምንም የጸጥታ ችግር ማከናወኗ አንዱ ሲሆን ይህም ዴሞክራሲን ከእኛ በላይ የሚያውቅ የለም ለሚሉ አገራት ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው።