ቀጥታ፡

ብሔራዊ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ውጤቱ ከዘላቂ የሠላም ስራዎች ጋር ጥብቅ ትስስር ይኖረዋል

መስከረም 22/2014 (ኢዜአ) ብሔራዊ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ውጤት ወንጀሎችን የመከላከልና የማስቀረት ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ከዘላቂ የሠላም ስራዎች ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።
 በጥናቱ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገራት የሸሹ ሀብቶቿን ለማስመለስ መከታተል እንድትችል ዕድል እንደሚፈጠርላትም ተናግረዋል።

በሠላም ሚኒስቴርና በዓለም ባንክ ትብብር አንድ ዓመት ከመንፈቅ የፈጀው የኢትዮጵያ ሁለተኛው አገራዊ የስጋት ተጋላጭነት ጥናት ሪፖርት ማብራሪያ መርሐ ግብር ትናንት ማምሻውን ይፋ ተደርጓል።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጥናቱ ከመንግስት፣ ከግል እና ከሙያ ማህበራት የተውጣጡ 60 የቴክኒክ አባላትን አካቶ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናቱ በ10 ክፍሎች የተሰራ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ዙሪያ ያሉ ስጋትና ተጋላጭነቶችን በሙሉ ለመሸፈን የሞከረም ነው ብለዋል። 

ጥናቱ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚገኙበትን ደረጃ ለማጥናትና ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ለማሟላት ያለመ ነው።

ሰፊና ጥልቅ ጥናት በመሆኑ የፖሊሲ ግብዓት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የጥናቱን ውጤት ወደ ፖሊሲና አገራዊ ዕቅድ መለወጥ ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ብለዋል።

አዲሱ መንግስት ከሚከውናቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል ወንጀልን መከላከልና መቆጣጠር አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በውጤቱም በአገሪቷ የሚገኙ የወንጀል አመንጪ ክፍተቶችን፣ ወንጀሎችና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎችን በስፋት እና በጥልቀት ማየት የቻልንበት ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።

በጥነቱ የተዳሰሱ ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው ከዘላቂ የሠላም ስራዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአገር ሉዓላዊነት እንዲቀጥል ከሚያደርጉ ጉዳዮች ቁልፉ የምጣኔ ሀብት ደህንነትን ማስጠበቅ በመሆኑ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ከባድ ወንጀሎች ለአገር ሕልውና ሲባል ደህንነታቸው መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል።

አገር ለማፍረስ ከሚሰሩ ኃይሎች እኩል የኢኮኖሚ ኣሻጥርና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመፍጠር የውንብድና አሰራሮች በመኖራቸው መሰል ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችሉ ሕጎች የማውጣትና ተቋማትን የማስተካከል ስራ ይሰራል ብለዋል።

ላለፉት 3 ዓመታት በተቋማት ሪፎርም ለአብነትም በፋይናንስ መረጃ ደህንነት ማዕከል የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማምጣታቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በገንዘብ እጥበትና ሽብርተኞችን የመርዳትና ሌሎች ወንጀሎች በዓለም ጥቁር መዝገብ ውስጥ ስሟ ሰፍሮ እንደነበረና ይህም ለኢንቨስትመንት ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር ሰፊ ርብርብ ተደርጎ ከጥቁር መዝገብ እንድትወጣና በዓለም አቀፍ ፋይናንስ መረብ ውስጥ እንድትገባ ማድረግ እንደተቻለ ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገራት የወጡ ሀብቶች እንዳሏት ተጨባጭ መረጃዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ ጥናቱ እንደ አገር የሸሹ ሀብቶችን ለማስመለስ መከተታተል እንድትችል ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በዚህም ወንጀልና ሕገ ወጥነትን በመከላከል ጤናማ ኢኮኖሚ ያለው አገር ለመገንባት መሰል ጥናቶች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም