ቀጥታ፡

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የፊታችን እሁድ ይመረቃል

አዲስ አበባ ነሃሴ 10/2010 በአዲስ አበባ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የፊታችን እሁድ በይፋ ይመረቃል። ጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም የተጀመረውና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በ37 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ፕሮጀክት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት ሙሉ ለመሉ በመንግስት ወጪ የተሸፈነው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የፊታችን እሁድ ይመረቃል። ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም የሚመረቀው ፕሮጀክቱ ከሳምንት በፊት በሙከራ ደረጃ ኃይል እያመነጨ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በአማካይ በዓመት 185 ጊጋ ዋት ሰዓት የሃይል ምርት እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ደረጃ በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነም አንስተዋል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተደረሰው ስምምነት ከከተማዋ ከሚወጣው 1 ሺህ 400 ቶን ቆሻሻ ለሃይል አቅርቦት ምንጭነት እንደሚውልም አመልክተዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ጠቁመዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታው በቆየባቸው ሶስት ዓመታት ለ 1 ሺህ 300 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ እድል እንደፈጠረም ገልጸዋል። በፕሮጀክቱ ላይ 286 የውጭ አገራት ዜጎች በግንባታው ላይ እንደተሳተፉና ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር እንደሰጡም ነው አቶ ምስክር የተናገሩት። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሚፈለገው ጊዜ ሃይል ማመንጨት ያልጀመረው የቦታ ርክክብና ግንባታውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ እቃዎች ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ያለው ሂደት በፈጀው ጊዜ ምክንያት እንደሆነም አመልከተዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከአካባቢ ተጽእኖ ነጻ የሆነና ኢትዮጵያ ታዳሽና አረንጓዴ ሃይል ለማግኘት የምታከናውናቸው እንቅስቃሴዎች አካል አንደሆነም አስገንዝበዋል። ፕሮጀክቱ ከሃይል ማመንጫነቱ ባለፈ ለስራው የሚውለው ቆሻሻ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ ጽዱና አረንጓዴ እንድትሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዋና ተቋራጭነት የእንግሊዝና የአይስላንድ ኩባንያ የሆነው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ፣ በንዑስ ተቋራጭነት ደግሞ የቻይናው ሲኤንኤኢሲ (CNAEC) የተሳተፉ ሲሆን የዴንማርኩ ራምቦል የተባለው ድርጅትም በአማካሪነት ሰርተዋል። ከሃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት ለመውሰድ የማስተላለፊያ መስመሮች በሚያልፍበት ቦታ የነበሩ መኖሪያ ቤቶችንና ሌሎች ንብረቶችን ለማንሳት የወሰደው ጊዜም ፕሮጀክቱ በተባለለት ጊዜ እንዳይጀመር አድርጎት እንደነበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ከአራት ወራት በፊት ለኢዜአ ገልጸው ነበር። ፕሮጀክቱን ከሚሰራው ስራ ተቋራጭ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ጋርም የተፈጠረው አለመግባባት ስራውን አዘግይቶት እንደነበርም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም