ቀጥታ፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለሰላም እና አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል

ደሴ/ደብረ በርሃን ፤ መስከረም 22/2014(ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት የወሎና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ጀማል ሰይድ፤ ኢትዮጵያ በአባቶቻችን ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንደኖረች አውስተዋል።  

ነጻነቷን በማስከበር ለአፍሪካ ብሎም ለመላው ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌትና ኩራት የሆነችው ኢትዮጵያ ህወሓት ለ27 ዓመታት ሲያራምደው በነበረው ከፋፋይ ፖለቲካ ህዝቦቿን በዘርና ቋንቋ ለያይቶ ሀገር ለማፍረስ ሲሰራ ቆይቷል ይላሉ ምሁሩ ።

ይህንን ተንኮልና ግፍ የተገነዘበው የኢትዮጵያ ህዝብ ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት በጋራ እያደረገ ላለው ርብርብ አድናቆት እንዳላቸው  ገልጸዋል።

አቶ ጀማል እንዳሉት፤ በቅርቡ አዲስ የሚቋቋመው መንግስት ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት ውስብስብ ችግር በመታደግ  በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት ለማምጣት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

"ወጣት አመራሮችንና ሀገር ወዳድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ በጋራ ማሻገር ያስፈልጋል" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሰላም፣ የዴሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ በበኩላቸው፤ አዲሱ መንግስት በህወሓት ዘመን የተበላሹትን ማስተካከል እንዳለበት ነው የተናገሩት።

"ህብረተሰቡ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ያለ ስጋት ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሀብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብቱ እንዲረጋገጥ አስተማማኝ ሰላም መፍጠርና የህዝቡን አንድነት ማጠናከር መንግስት የመጀመሪያው ተግባሩ መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ  ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ማቋቋም፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መጠገንና ወደልማት ስራው መመለስ እንዳለበትም አመልክተዋል።   

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቃት ያላቸውን በመሾም ሀገርና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ እድል መስጠቱ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በእዚህ በኩል ክልሎች ያሳዩት ጅምር በቀጣይም እንዲጠናከር አሰተያየት ሰጥተዋል።

ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ ከመጠበቅና አንድነቱን ከማጠናከር ባለፈ የአሸባሪውን ህወሓት ቡድን ዕድሜ ለማሳጠር በተለያየ መንገድ የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ተናግረዋል

አዲስ በሚመሰረተው መንግስት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት አባል ከሆኑ ብዝሃነትን ለማስተናገድ ከማስቻሉ ባለፈ ሃገሪቱን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

"አዲስ የሚቋቋመው መንግስት ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አበክሮ ሊሰራ ይገባል'' ያሉት ደግሞ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዶክተር አስማማው አዳነ ናቸው።

እንደ ምህሩ ገለጻ ፤ በየጊዜው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ከህዝብ ጋር በትብብር መስራት ከአዲሱ መንግስት ይጠበቃል።

የሚመሰረተው መንግስት ወራሪውን የህወሓት ቡድን ፈጥኖ በመደምሰስ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና ዜጎች ያለስጋት ተንቀሳቅሰው ሀብትና ንብረት ማፍራት እንዲችሉ ማድረግ አንዳለበትም እንዲሁ።

"መንግስት ሲመሰረት በቅድሚያ የሀገር ሰላምና በልጽግናን እንጠብቃለን" ያሉት ደግሞ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ታደሰ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከገጠማት ውስብስብ ችግር ፈጥኖ ለማውጣትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በቁርጠኝነት መስራት የግድ መሆኑን ተናግረዋል።

የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በክልሎች የመንግስት ምስረታ የተጀመው አሳታፊ የምክር ቤት አደረጃጀት በፌደራል ደረጃም መተግበር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም