ቀጥታ፡

በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

ደሴ ፤ መስከረም 22/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ወረራ ከሰሜን ወሎ ዞን ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሰይድ የሱፍ እንደገለጹት፤ ድጋፉን ያደረጉት ነጃሽ በጎ አድራጎት ማህበር፤ ባዩሽ መስጅድ እንዲሁም  በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የወሎ ተወላጆች ናቸው።

ከድጋፉ 600 ኩንታል ዱቄት፤ 95 ኩንታል ማካሮኒ፤130 ኩንታል ሩዝ ይገኝበታል።

እንዲሁም 230 ካርቶን ፓስታ፤ 250 ካርቶን ዘይትና አልባሳት በድጋፉ ውስጥ ተካተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የባዩሽ መስጅድ ህብረተሰቡንና የመርካቶ ነጋዴዎችን በማስተባበር  የምግብ እህል፣ ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ወደ ከተማዋ የሚገቡት ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ድጋፉ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ድጋፍ ላደረጉት አመስግነው፤ ይህም በደሴ ለተጠለሉት ብቻ ሳይሆን ጫካ ውስጥ የቀሩትንም ያካተተ በመሆኑ ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት።

አሸባሪው  ህወሓት  በህዝብ ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ከመፈጸሙም ባለፈ የሚችለውን እየዘረፈ ያልቻለውን ደግሞ እንሰሳት እንኳ ሳይቀር እያወደመ በመሆኑ  የቡድኑ እድሜ ለማሳጠር  የኢትዮጵያ ህዝብ  አንድነቱን አጠናክሮ ድጋፉን  እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በድጋፉ ርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ የሰሜን ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም  የሐይማኖት አባቶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም