የአረጋውያን ማህበራዊ ጥበቃ እውን ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የአረጋውያን ማህበራዊ ጥበቃ እውን ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አዳማ፤ መስከረም 22/2014 (ኢዜአ) የሀገር ባለውለታ አረጋውያን ማህበራዊ ጥበቃ እውን ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።
30ኛው አለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን "ሁሉ አቀፍ ማህበራዊ ጥበቃ ለአረጋውያን " መሪ ሀሳብ በአዳማ ገልመ አባገዳ ተከብሯል።
ሚኒስትሩ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋዊያን ታፍረውና ተከብረው እንዲኖሩ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው።
በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመሩ የማዕድ ማጋራትና የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት የትኩረቱ አንድ አካል ነው ብለዋል ።
የአረጋዊያንን ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ፖሊስ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በልማታዊ ሴፍቲኔት አረጋዊያን ተጠቃሚ እንዲሆኑና መሰረታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በዘርፍ የሚሰሩ ማህበራትን በፋይናንስና ገቢ ምንጮች ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሀገርን አንድነት ጠብቆ ላስረከቡን አረጋዊያን ህይወት መሻሻል፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአረጋዊያንና ጡረተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አባ ሙዳ አበበ ሃይሉ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አረጋዊያን እንደሚገኙ ጠቅሰው የአረጋውያን ህይወት ለማሻሻልና ተስፋቸው እንዲለመልም ለማስቻል እየሰራን ነው ያሉት።
በተለይ ከለውጡ ወዲህ የአረጋውያን ተስፋ እንዲለመልም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል ።
የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ከማደስ ጀምሮ የተለያዩ የበጎ ተግባር አገልግሎቶች እንዳሉ ተናግረዋል።
ለሀገር ሰላምና አንድነት ሁሉም በጋራ እንዲቆም ያመለከቱት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ የሀገሪቱ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት እንዲጠናክር ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል ።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ዘርፍ ኮሚሽነር ወይዘሮ እርግብ ግብረሃዋርያ፤ ወቅቱ በህዝብ ይሁንታ የተመረጠው መንግስት የሚመሰረትበት በመሆኑ የአረጋውያን ህይወት ይለወጣል የሚል እምነት አለን ብለዋል ።
በተለይ ለአረጋውያን ህይወት መሻሻል የማህበራዊ ደህንነት ፖሊሲና ልማት ውጤታማ እንዲሆን ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ክብርና ስብዕና የተላበሰ ሁሉን አቀፍ አገልግሎትና እንክብካቤ እንዲያገኙ መንግሥት በትኩረት መስራት እንደሚገባው አመልክተዋል ።
በተለይ ለአረጋዊያን ሰብዓዊ መብቶች መስፋፋትና መከበር ብሎም ዘላቂ የሆነ መሰረታዊ አገልግሎት እንዲኖራቸው ብሎም ድምፃቸው እንዲሰማ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።