ቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾችን አለመተግበር የግዢ ስርዓቱ ችግር እንዳይፈታ አድረጓል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾችን አለመተግበር የግዢ ስርዓቱ ችግር እንዳይፈታ አድረጓል ተባለ
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 የቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾችን ተግባራዊ አለማድረግና የአደረጃጀት መላላቶች የመንግስትን ግዢና ንብረት አያያዝ ስርዓት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆን እንዳደረገው የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ይህን ያለው ዛሬ ባካሄደው ጉባኤው ላይ ነው ። በጉባኤው ላይ የፌዴራልና የክልል ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት "ህብረተሰቡ ከመንግስት ከሚወጣው በጀት አንፃር ተገቢውን አገልግሎት እያገኘ አይደለም"። ዋና ዳይሬክተሯ በምክንያት ያነሱት ደግሞ "የሚፈፀመው ግዢ የተጓተተና በአግባቡ ስርዓቱን ተከትሎ የሚፈፀም አለመሆኑን ነው"። ይህን ችግር ለመፍታት የግዢ ስርዓቱን በውጤት ለመለካት የሚያስችሉ መመዘኛ መስፈርቶችን የያዘውን የቁልፍ አፈፃፀም አመላካች (ኬ ፒ አይ) ስርዓት በአራት ክልሎችና በ 7 የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከ2008 ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም አተገባበሩ ዝቅተኛ ነው። የትግራይና ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኬ ፒ አይን ተግባራዊ በማድረግ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አፈፃፀምን መለካት የጀመሩ ሲሆን በተቃራኒው ኦሮሚያና አማራ በሚፈለገው ልክ ወደ ተግባር አልገቡም ተብሏል። ይህን ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ባልቻሉት ክልሎች የተነሳ አገሪቱ ከውጪ ተቋማት በእርዳታ ታገኝ የነበረውን ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር እንድታጣ አድርገዋታል። በሌላ በኩል ተቋሙ ያለው አደረጃጀት ወጥነት የሌለውና የሰው ኃይሉም በቁጥርም ይሁን በአቅም ክፍተት ያለበት መሆኑ በስራው ጥራት ላይ አሉታዊ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ ነው የተነገረው። የኤጀንሲው የግዢ አስተባባሪና የስልጠና አማካሪ አቶ ፀጋዬ አበበ እንደሚሉት ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን በጀት ወጪ የሚያደርገው የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ቢሆንም የሚሰጠው ግምት አናሳ በመሆኑ የሚፈለገውን ተግባር እየተወጣ አይደለም። ለአብነትም 167 ወረዳዎች ያሉት የአማራ ክልል በተቋሙ ያለው 3 የሰው ኃይል ብቻ መሆኑን በማንሳት የችግሩን ጥልቀት አሳይተዋል። አደረጃጀቱ ያልተሟላ ከመሆኑና አዳዲስ ስርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው የፍላጎት ማነስ የግዢ ኦዲት ሪፖርቶችን በወቅቱ ላለማቅረብም ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በተጨማሪም ተገቢው ሰነድ ተደራጅቶ እንዳይቀመጥም አድርጓል። ችግሮቹን ለመፍታት የግዢ መዋቅሩ የሚይዘውን የሰው ኃይል በቁጥርም ሆነ በጥራት ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል። የሚመለከተው አመራርም በ'ኬ ፒ አይ' ላይ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት ተግባራዊ እንዲያደርግ ማበረታታት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የግዢና የንብረት አያያዝና አስተዳደር ስርዓቱን ለማስተካከል ተጠያቂነትንም ማስፈን እንደሚገባ ጠቁመዋል።