ቀጥታ፡

የዝክረ መለስ ስድስተኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክቶ ሃገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ ሊካሄድ ነው

መቀሌ ነሀሴ 10/2010 ስድሰተኛው ዓመት የዝክረ መለስ መታሰቢያ ስነስርዓት ምክንያት በማድረግ ሃገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ እንደሚካሄድ የትግራይ የፖሊስ ጥናት ተቋም ገለጸ፡፡ መድረኩን የሚያዘጋጁት ተቋሙ  ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው። የተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፍስሃ ሃብተፅዮን ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ፣በውይይት መድረኩ  በአቶ መለስ ዜናዊ  የመነጩ የፖሊሲና   የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስተሳሰቦችን ለኢትዮጰያ ያላቸው  ፋይዳ  በስፋት ይዳሰሳል። የመለስ አስተሳሰቦችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ለትውልድ እንዲተላለፉ በትጋት ለመስራት መድረኩ ምቹ ሁኔታ ይኖረዋል። " በፌዴራል ስርዓት አስተሳሰብና አተገባበር፣በሰላምና ደህንነት ጉዳይ ፣ በአፍሪካ የፀጥታ ጉዳዮች የነበረው ሚና በመድረኩ ይዳሰሳሉ "ብለዋል። የአረንጓዴ ልማት እሳቤዎች ለአካባቢ ድህንነት የነበራቸው አስተሳሰብና ጥብቅና  ውይይት እንደሚደረግባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የውይይት መድረኩ አቶ መለስ  የቀየሷቸው ፖሊሲዎች ለሀገሪቱ  ህዝብ  የልማት ጉዞ የነበራቸው ፋይዳ ቀጣይነት እንዲኖራቸውና በስራ ሂደት የታዩባቸው  ክፍተቶችን ለመለየት   ያግዛል ተብሏል። በመቀሌ  ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የውይይት መድረኩ አስተባባሪ አቶ መረሳ ፀሐዬ  በበኩላቸው፣ መድረኩ " በተለይ የመለስ ዜናዊን ራዕይ በኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ በሚል አጀንዳ ትኩረት ያደርጋል "ብለዋል። አዲሱ ትውልድ በሀገር ግንባታ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ መለስ ዜናዊ አስተሳሰቦች  የነበራቸው አስተዋፅኦ ለመቃወም ሆነ ለመደገፍ የተሻለ እውቀት እንዲኖረው ይረዳል። የመለስ አስተሳሰቦች ለማስረፅና ለማሻሻል እንዲቻል መድረኩ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ መረሳ አመልክተዋል። በመጪው እሁድ በሚካሄደው የውይይት መድረኩ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ክልል ያሉ ነባርና አዳዲስ አመራሮች ፣በፖሊሲ ጥናት፣ በምርምርና አስተዳደር የሚሰሩ አካላት ፣የተለያዩ አደረጃጀት ተወካዮችና ምሁራን ጨምሮ ከ2ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም