ቀጥታ፡

የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ወደ ባንክ አደገ

ሀዋሳ ፤ መስከረም 21/2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር ዛሬ ባካሄደው የመጀመሪያው የመስራቾች ጠቅላላ ጉባኤ በይፋ ወደ ባንክ ማደጉ አስታወቀ።
የአክሲዮን ማህበሩና የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በወቅቱ እንዳሉት፤  ማይክሮ ፋይናንስ የነበረውን ወደ ባንክ ያደገው መንግስት የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝና  የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ነው።

ወደ ባንክነት ለማደግ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያስቀመጠውን አደረጃጀት፣ አፈጻጸም፣ የሰው ሃይል፣ የካፒታልና ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላቱን ገልጸዋል።

በዚህም የመጀመሪያ የመስራቾች ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ማይክሮ ፋይናንሱ በይፋ ወደ ባንክነት ማደጉን አስታውቀዋል።

የ"ሲዳማ ባንክ" ዘመናዊ የባንክ አሰራሮች በማከል በአነስተኛ ደረጃ የሚሰጠውን ብድር ጨምሮ ሁሉንም የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆኑንም አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።

ማይክሮ ፋይናንሱ ወደ ባንክነት ማደግ መቻሉ በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችል በኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማገዝ እንደሚረዳ ተመልክቷል።

የሲዳማ ባንክ አክሲዮን ማህበር የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳዊት ቲቦ፤ የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ ከ23 ዓመታት በፊት  ከ4 ሚሊዮን ብር ባልበለጠ ሀብትና በጥቂት ሰራተኞች ወደ ስራ የገባ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ አክሲዮን ማህበሩ 570 ሚሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሀብት እንዳለው ጠቅሰው፤  ዓመታዊ የብድር አቅሙንም 300 ሚሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

በ60 ሰራተኞች የጀመረውን አክሲዮኑ አሁን ላይ ከ300 በላይ  እንዳሉት አቶ ዳዊት ጠቁመዋል።

አክሲዮን ማህበሩ አካታች በሆነ መልኩ መላውን የክልሉ ነዋሪዎች በማገዝ በተለይም መስራት እየፈለጉ የአቅም ውስንነት ያላቸውን ዜጎች በማገዝ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

ማህበሩ በካፒታልና በጠቅላላ ሀብት ወደ ባንክነት በማደግ የአገልግሎት አሰጣጡን በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

ባንኩ አሁን ላይ ባገኘው ፈቃድ መሰረት ዝቅተኛውን መስፈርት በማሟላት በይፋ የመስራቾች ጉባኤ እያካሄደ መሆኑን አመልክተው፤ የአክሲዮን ሺያጩን በማጠናከር መደበኛ የባንክ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

አክሲዮን ማህበሩ በ30 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና  ወደ ባንክነት ለማደግ ባለው ሽግግር ውስጥ ከ1 ሺህ 800 በላይ ባለ አክሲዮኖች  እንዳሉት ተጠቁሟል።

ከባለአክሲዮኖች መካከል አቶ ብርሃኑ ቱንሲሳ በሰጡት አስተያየት፤  ለረጅም ጊዜያት ከአክሲዮን ማህበሩ ብድር በመውሰድ ስራቸውን አስፍተው በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ወደ ባንክነት ማደጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የሲዳማ ባንክ ምስረታ ጉባኤ ላይ ባለ አክሲዮኖች  የፌደራልና ክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም