ቀጥታ፡

በሰብአዊ እርዳታ ስም የሚፈጸምን ያልተገባ ተግባር መከላከል የመንግስት ዋና ሃላፊነት ነው

ጎንደር፤መስከረም 21/2014(ኢዜአ) ከተልዕኳቸው ውጪ በሰብአዊ እርዳታ ስም ያልተገባ ተግባር ላይ የሚሰማሩ አካላትን ለመከላከል በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ መኳንንት ዱቤ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ እአአ በ1945 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማቋቋሚያ ኮንቬንሽን የወጣውን ህግ መሰረት ያደረገ ነው፡፡

ኮንቬንሽኑ ማንኛውም ዲፕሎማትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ በአንድ ሀገር ሉአላዊነትና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ወንጀል ከፈፀመ የተሰጠውን ከለላ በማንሳት ከሀገር እንዲባረር እንደሚደነግግም ተናግረዋል፡፡

“አለም አቀፍ ድርጅቶቹ በሰብአዊ እርዳታ ስም የተቋቋሙ መሆናቸው ቢታወቅም በተዘዋዋሪ የአሜሪካንን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ተልእኮ በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው” ብለዋል፡፡

“ድርጅቶቹ ከምእራባውያ ተጽእኖ ነፃ ያልወጡና የእነሱ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ናቸው” ያሉት አቶ መኳንንት፤የአሜሪካ መንግስትና ተከታዮች ፍላጎት ደግሞ ህወሃትን ማዳን ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ 

“አለም አቀፍ መርሆዎችን አክብረው መስራት ሲገባቸው ከተሰጣቸው ተልእኮ ውጪ በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሲንቀሳቀሱ መንግስት እርምጃ መውሰዱ ተገቢና ወቅታዊ ነው” ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ስለሺ ዋለልኝ ናቸው።

“መንግስት የሀገሪቱን ህግ የጣሱ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅት ሰራተኞችን የማባረር ስልጣን አለው” ያሉት መምህሩ፤ ከዚህ ቀደም ከህገ-ወጥ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጥ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

“መንግስት የወሰደውን ከሀገር የማባረር እርምጃ ፈጥነው ለማውገዝ አሁን ላይ የተጣደፉ አካላት የህወሃት የሽብር ቡድን የፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ አንድም ጊዜ ቢሆን ፈጥኖ ለማውገዝ ያልደፈሩ ናቸው” ሲሉም ነው የተናገሩት።

በሀገር ሉአላዊነት፣ በህዝብ ጥቅምና ደህንነት ላይ አደጋ የሚጥል ተልእኮ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ መንግስት በማንኛውም ጊዜ እርምጃ የመውሰድ መብት አለው ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አንዳርጋቸው ተስፋሁን ናቸው፡፡

መሰረታዊው የመንግስት ግዴታ ህዝብን ከአደጋ መታደግ ብሎም ሀገርን ከውጪ ወራሪም ሆነ ከውጪ ጣልቃ ገብነት መከላከል መሆኑን ጠቅሰው፤ “መንግስት ባደረገው ግምገማ መሰረት ውሳኔ ላይ መደረሱ ተቀባይነት አለው” ብለዋል፡፡

በሰብዓዊ እርዳታ ስም ያልተገባ ተግባር ላይ የተሰማሩና በአለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰባት ሰራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግስት ትላንት ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም