ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ከፌደራል መንግስትና ክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው

አዲስ አበባ መስከረም 21/2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ከፌደራል መንግስትና ክልሎች ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሐሰን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አሻድሊ ሐሰን እንደገለጹት፤ ባለፈው ዓመት በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ በክልሉ በአንዳንድ አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች መከሰታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም አሸባሪው ሕወሓት ቡድን በሚያሰማራቸው ተላላኪዎችና ቅጥረኞች ክልሉን የግጭት ቀጠና ለማድረግ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አውስተዋል።  

በዚህም በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ መጋለጣቸውን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከፌደራል መንግስትና ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የጸጥታው ሁኔታ በእጅጉ መሻሻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ርዕሰ መስተዳደሩ ጨምረው የገለጹት።

በተለይም ክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚከናወንበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጸጥታ አካላት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተቀናጅተው ሰላምን በማስፈን ረገድ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል አዲስ የሚመሰረተው የክልሉ መንግሥትም ሰላም ከማስፈን ጎን ለጎን የክልሉን ነዋሪዎች ተጠቃሚ በሚያደርጉ  የማልማት ስራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጀት በመስራት በአስር ዓመት እቅድ ውስጥ የተካተቱ ተግባራትን በተቀመጠላቸው ጊዜ ሰሌዳ ገቢራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም እንዲሁ።  

በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት መሆኑን አንስተው በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለኃብቶች ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም