ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ከተለያዩ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራች ነው

74

አዲስ አበባ መስከረም 21/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ከተለያዩ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስርዓቱን ለማጎልበት ያግዛሉ ባላቸው መስኮች ዙሪያ ሚኒስቴሩ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

የኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ያንያ ሰዒድ፤ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መስራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኩ ተቋማትና ድርጅቶች በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በትብብር የሚሰሩበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያስቀመጠቻቸውን የልማት ዕቅዶች በቴክኖሎጂ በመታገዘ ተግባራዊ እንድታደርግ ሌላው የምክክሩ አላማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሚኒስቴሩ የኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍ ዳሬክተር አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፤ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ድጋፍ ሊደረግባቸው የሚገቡ መስኮች ተለይተው ከዓለም አቀፍና አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋልም ብለዋል።

የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ የልማት አጋሮች፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች በፈጠራ አቅም ያላቸውን ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችና የዘርፉ ስራ ፈጠራ እያደገ መምጣቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም