ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በጣቢያዎች ደረጃ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ እየተደረገ ነው

ዲላ/ሚዛን/አርባምንጭ/ሆሳዕና/ጂንካ፤ መስከረም 21/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ትናንት ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ ጊዜያዊ ውጤት ለሕዝብ ይፋ እየተደረገ ነው።

በደቡብ ክልል ሰኔ 14/2013ዓ.ም. ምርጫ ባልተካሄደባቸውና ድጋሜ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወሰነው መሰረት ትናንት ተከናውኗል።

በዚህም የምርጫ ጊዜያዊ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ይፋ እየተደረገ ይገኛል።

ጊዜያዊ ውጤቱ በጌዴኦ ዞን ቡሌ ምርጫ ክልል፣ በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮና ጉራፈርዳ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ በሀድያ ዞን አራት የምርጫ ክልሎች፣ በጋሞ ዞን ብርብር የምርጫ ክልል እንዲሁም በደቡብ ኦሞ ዞን ስድስት የምርጫ ክልሎች ሥር በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች መለጠፉን የኢዜአ ሪፖርተሮች ከየሥፍራው ዘግበዋል።

የብርብር ምርጫ ክልል ሃላፊ ወይዘሮ አዲስዓለም ጥላሁን እንዳሉት፤ ትናንት ምርጫው ያለምንም ችግር መጠናቀቁን ተከትሎ ቆጠራ በማድረግ ዛሬ በምርጫ ጣቢያዎች ደረጃ እየተለጠፈ ነው።

በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ የተደረገው የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በየጣቢያው ይፋ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም