ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ ለማላቀቅ በቁርጠኝነት እንሰራለን

ባህር ዳር ፤ መስከረም 21/2014(ኢዜአ) ክልሉ በአሸባሪውና ወራሪው ህወሓት ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ ተላቆ ወደ መደበኛ የልማት ሥራው እንዲገባ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አዲሶቹ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
ከአባላቱ መካከል አቶ ጥላሁን ደጀኔ፤ በአሁኑ ወቅት ክልሉ የገጠመው አደጋ ውስብስብ መሆኑን ገልጸዋል።

ወራሪውን የህወሓት የጥፋት ቡድን በመመከት ህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ የአመራር አንድነትና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

"ህዝቡ ይሁንታውን ሰጥቶ ስለመረጠን በምክር ቤቱ ምስረታ ሁላችንም በድምጹ የሰጠንን አደራ በብቃት በማገልገል ለመወጣት ቃል ገብተናል" ብለዋል።

ድል ያለመስዋዕትነት እንደማይገኝ የገለጹት አቶ ጥላሁን፤ ወራሪውን የጥፋት ቡድን በጋራ በመመከት ህዝቡን ከገጠመው ችግር ለማላቀቅ በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ጥላሁን እንዳሉት፤ የአሁኑ ወቅት ህዝቡ ከመከፋፈል ወጥቶ ወደአንድነት የመጣበትና የገጠመውን የህልውና አደጋ በጋራ ለመመከት አቋም የያዘበት ነው።

"እንደ ምክር ቤት አባልነቴ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ህዝቤን ከችግር የሚያወጣና ነጻነቱን የሚያስጠበቅ ሥራ ለመስራት ተዘጋጅቺያለሁ" ብለዋል።

"ህዝባችን በወራሪው የህወሓት አሸባሪ ቡድን የህልውና አደጋ ውስጥ ይገኛል'' ያሉት ሌላው የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አድና ምህረቱ ናቸው።

በወራሪው ቡድን በርካታ ቁጥር ያለው የክልሉ ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሎ ለችግር መጋለጡን ገልጸው፤ "ይህን አጥፊ ቡድን ከገባበት ገብቶ ለመደምሰስ ህብረታችንን እናጠናክር" ብለዋል።

"የአማራ ህዝብና ክልሉ የገጠመውን  አደጋ ለመመከት አንድነታችንን በማጠናከር፣ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆምና ህዝብን በማነቃቃት የራሳችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል" ሲሉም አክለዋል።

ሌላው የምክር ቤት አቶ አየነው ተመስገን በበኩላቸው፤ "የአማራን ህዝብ ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ የሚያወጣ በሳል አመራር የሚፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።

አዲስ የተመሰረተው የክልሉ መንግስት ህዝቡን ከችግር ለማውጣት በሚያከናውናቸው ተግባራት የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

"ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ አንድነታችንን በማጠናከር በህልውና አደጋ ውስጥ ያለውን ህዝባችንን ሰላም በዘላቂነት ማረጋጋጥ ይገባናል፤ እኔም ሌት ተቀን በመስራት ሀላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

ህዝቡን በማስተባበር ወረራውን ኃይል አስወግዶ ወደልማት እንዲገባ መስራት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደነበሩበት ቄያቸው መመለስና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በማድረግ በኩል አዲስ ከተመሰረተው መንግስት ብዙ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።  

የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር መስራች ጉባኤ ትናንት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና የምክር ቤቱን አፈ-ጉባኤ ጨምሮ ሌሎች አስፈፃሚዎችን በመምረጥ መጠናቀቁን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም