በቡና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጠው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጠው ጠየቁ
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 የኢትዮጵያ የቡና ምርት ከግብይት ጀምሮ ውስብስብ ችግሮች ስላሉበት መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ጠየቁ። ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት "የቡና ልማት ግብይት፣ ዕድል፣ ዋና ዋና ማነቆዎችና መፍትሄ አማራጮች" በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ውይይት ተደርጓል። የዘርፉን ስራ የሚመሩ መንግስታዊ የስራ ኃላፊዎች፣ ቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ማሕበራት ተወያይተዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች የቡና ጉዳይ ማዕከላዊ በሆነ መልኩ በአንድ መስሪያ ቤት የሚመራ ሳይሆን በስድስት መስሪያ ቤቶች ለዘርፉ አንቀሳቃሾች አገልግሎት መስጠቱ ችግር እንደሆነ አንስተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የቡና አምራቾች ለተለያዩ የጸጥታ ችግሮች መጋለጣቸውም ሌላው ስጋት መሆኑ ተገልጿል። ዘርፉ ራሱን በማስተዋወቅ ረገድ አሁንም ገና መሆኑና የኢትዮጵያን ቡና የሚያስተዋውቅ መለያ አለመኖርም እንደ ችግር ተነስቷል። በውይይቱ ወቅት መነሻ ገለጻ ያቀረቡት የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ዘርፉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለ30 ሚሊዮን ሰዎች መተዳደሪያ፤ 40 በመቶ ገደማ የሚሆን የውጭ ምንዛሪም ማግኛ ነው። በአማካይ በየዓመቱ የቡናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት ገቢ 25 በመቶውን ድርሻ እንደሚያዝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ በችግሮች የተተበተበ በመሆኑ የሚመረተው አነስተኛ፣ የሚላከው ዝቅተኛና የሚያስገኘውም ገቢ ካለው አቅም አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህ እንደ ዋና ችግር ሊጠቀሱ የሚችሉት የቡና ህገ-ወጥ ንግድና ፍትሃዊነት የጎደለው ንግድ፣ እሴት ያለ መጨመር፣ ቡናን በዝቅተኛ ዋጋ መሸጥ፣ ዘርፉ ከደላሎች ጀምሮ ለብልሹ አሰራር መጋለጥ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ችግሮቹ ይፈቱ ዘንድ ከሁሉም በላይ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን መጠቀምና እሴት መጨመር በዋናነት ይተግበሩ ሲሉም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቡና ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ መንግስት ከዘርፉ አንቀሳቃሾች ጋር በቅርበት ይሰራል ብለዋል። በተለይም ዘርፉ ለ15 ዓመታት የአንድ ኩንታል ጭማሪ ዕድገት እንኳን አለመሳየቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በኩባንያ መልክ ቢንቀሳቀሱ የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል። ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተጠናክሮ ዘርፉን እንዲመራ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል። ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘም መንግስት የሚሰራው ስራ እንዳለ ሆኖ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸው ባለበት አካባቢ የሚገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። መንግስት የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ያሉ ሲሆን የዘርፉ አንቀሳቃሳሾች ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እንዲሰሩ አሳስበዋል። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችም የኢትዮጵያ ቡና መለያ እንዲያዘጋጁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ሰንዝረዋል። ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከላከችው 238 ሺህ 465 ሜትሪክ ቶን ቡና 838 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን ይህም ከ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት አንጻር የ44 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል። ምርቱ ከ60 በላይ ለሚሆኑ አገራት የተላከ ሲሆን ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ ዋነኛ መዳረሻዎች ናቸው።