አገር በቀል እውቀቶችንና የግጭት መፍቻ እሴቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አስተሳስሮ ለትውልድ ማስተማሪያ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አገር በቀል እውቀቶችንና የግጭት መፍቻ እሴቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አስተሳስሮ ለትውልድ ማስተማሪያ ማድረግ ይገባል
አዲስ አበባ ፣መስከረም 21/2014(ኢዜአ) አገር በቀል እውቀቶችንና የግጭት መፍቻ እሴቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አስተሳስሮ ለትውልድ ማስተማሪያ ማድረግ እንደሚገባ የብሄራዊ እርቀ-ሰላም ኮሚሽን ገለጸ።
ከ320 በላይ አገርበቀል የእርቅ ዘዴዎችን ለጥናትና ምርምር ማዘጋጀቱንም አስታውቋል።
የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለይም በፖለቲካ ምክንያት እየተሸጋገሩ የመጡ ቁርሾዎችን ለማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ለማውረድ ታህሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወሳል።
የኮሚሽኑ አባላት አንጋፋዎቹ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ደበበ ሰይፉ እና አያልነህ ሙላቱ በዚሁ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኮሚሽኑ አባል አያልነህ ሙላት፤ "የኢትዮጵያውያን ችግር በራሳቸው በኢትዮጵያውያን እንጂ በሌሎች አገሮች መፍትሔ ሊገኝለት አይችልም"ብለዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ በእያንዳንዱ አካባቢ ያለውን በጎ ልማድና ባህላዊ የእርቀ-ሰላም ዘዴ በሳይንሳዊ ዘዴ አስተሳስሮ መጠቀም ወቅቱን የዋጀ መፍትሔ ይሆናልም ነው ያሉት።
አገር በቀል እውቀቶችንና የግጭት መፍቻ እሴቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አስተሳስሮ ለትውልድ ማስተማሪያ በማድረግ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት አገር በቀል ዕውቀቶችን መነሻ አለማድረጉ ለችግሮች አንዱ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት አገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ማስተሳሰርና ትውልዱን ማስተማር እንደሚገባ ተናግረዋል።
እርቀ ሰላም በአንድ ተቋም የሚፈጸም ባለመሆኑ ከግለሰብ ጀምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸውም አባላቱ አሳስበዋል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደበበ ሰይፉ፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ ወቅታዊ ግጭቶች ሲፈጠሩ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጥ አለመሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜያት የነበሩ ቂምና ቁርሾዎችን ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙና እውነተኛ እርቅ እንዲመጣ በትኩረት የሚሰራ ተቋም ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በተለይም አገር በቀል የግጭት አፈታትና የእርቅ ዘዴዎችን በመጠቀም "ለኢትዮጵያዊያን የዘላቂ ሰላም መሰረት ለመጣል ኮሚሽኑ ይሰራል" ብለዋል።
በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የግጭቶችን መነሻዎች በጥናት በመለየት ለጥናትና ምርምር ዝግጁ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።