“ሀገር ለቀው እንዲወጡ በታዘዙ የውጭ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፣ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው” - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
“ሀገር ለቀው እንዲወጡ በታዘዙ የውጭ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፣ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው” - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
መስከረም 21/2014 (ኢዜአ) በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ከተሰማሩበት ዓላማ ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሰባት የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፣ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡
በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ 7 ሠራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዘዙን ተከትሎ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ግለሰቦቹ ከሀገር እንዲወጡ የታዘዙት ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ሲንቀሳቀሱ እና በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው።
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፣ ማንኛውም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋምም ሆነ ግለሰቦች ሲገቡ ፈቃድ አላቸው፤ የሚሰሩትም በፈቃድ ነው።
የትኛውም ተቋም እና ግለሰብ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ ተግባሩ ሕገ-ወጥ ነው፤ ከሀገር እንዲወጡ በታዘዙት ግለሰቦች የሆነውም ይኸው ነው፡፡
“አንዳንዱ ለሕክምና ሥራ እና ለጤና አገልግሎት ይመጣና፣ ጤናን በሚያዛቡ እና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ተግባራት ላይ ይሰማራል፤ ለውኃ ቁፋሮ ይመጣና ሀገር ሲቆፍር ይውላል፤ ይህ ዓይነት ተግባር ደግሞ በየትኛውም ሀገር አይፈቀድም፤” ያሉት አምባሳደር ዲና፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላም ሀገር የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት፣ የአንድን ሀገር ደህንነት፣ የአንድን ሀገር ሰላም የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ክልክል መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
መንግሥት ደግሞ እነዚህን ኃይሎች የማስቆም ኃላፊነት ያለበት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃም በዚህ መሠረት የተወሰደ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት(ኢፕድ) እንደዘገበው እነዚህ አካላት ይማራሉ፣ ከስህተታቸው ታርመው ይመለሳሉ በሚል መንግሥት ትዕግሥት ማሳየቱን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።
ይህ መልካም ቢሆንም እነርሱ ይህን ተገንዝበው ያለመታረማቸው አሳዛኝ ነው፤ በመሆኑም ከዚህ ሁሉም ትምህርት ሊወስድበት ይገባል ሲሉ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።