ቀጥታ፡

የመጀመሪያ ልጅ መውለጃና ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የመሳተፍ ግጥምጥሞሽ

መስከረም 20/2014( ኢዜአ )  ሲትራ መሐመድ በአዲስ አበባ የሐረሪ ክልል ተወላጆች ድምፅ ከሚሰጡባቸው ምርጫ ጣቢያዎች መካከል በሆነው ጀሞ ምርጫ ጣቢያ ድምፅ ለመስጠት ተገኝታለች።
ታዲያ በምርጫ ጣቢያው ከተገኙት ድምፅ ሰጪዎች መካከል ሲትራን ምን ይለያታል? ቢሉ ሆዷ ገፍቶ ልትወልድ መቃረቧ፤ እርግዝናዋን በሚከታተለው ሐኪምም ዛሬ እንደምትወልድ የተነገራት መሆኗ ነው።

ሲትራ የመጀመሪያ ልጇን የምትወለድበትና ለመጀመሪያ ጊዜም የምርጫ ድምፅ የምትሰጥበት ቀን መገጣጠም አግራሞትን ፈጥሯል።

በሐረሪ ክልል ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ መካሄድ ነበረበት።

ይሁንና የሐረሪ ክልል መንግሥት ከክልሉ ውጭ ያሉ ተወላጆች ድምፅ መስጠት ይችላሉ ሲል፤  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 'ሐሳቡ ሕጋዊ ተቀባይነት የለውም በማለቱ ሳይካሄድ ቆይቷል።

ክልሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶት በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የተካሄደው ክርክር ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ችሎቱ ከሐረሪ ክልል ውጭ ያሉ ዜጎች ድምፅ የመስጠት ሕጋዊ መብት እንዳላቸው በመግለጽ ድምፅ እንዲሰጡ ውሳኔ አሳልፏል።

በውሳኔው መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሐረሪ ክልልና ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ዜጎች ዛሬ ድምፅ እንዲሰጡ የዛሬን ቀን መቁረጡ የሚታወስ ነው።

ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሐረሪ ተወላጆች ስድስት ምርጫ ጣቢያዎችን ያደራጀ ሲሆን፤ ተወላጆቹ ዛሬ ከማለዳው 12፡00 ሠዓት ጀምሮ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ኢዜአ በጀሞ ምርጫ ጣቢያ በነበረው ቆይታ ድምፅ ሲሰጡ ካገኛቸው መራጮች መካከል የመጀመሪያ ልጇን ዛሬ እንደምትወልድ በሐኪሟ የተነገራት ሲትራ መሐመድ ትገኝበታለች።

ሲትራ ዛሬ ልጇን ለመውለድ ሆስፒታል ቀጠሮ ያላት ቢሆንም፤ ከምወልደው ልጄ አገር ይቀድማል ብላ ድምጿን ለመስጠት በምርጫ ጣቢያ መገኘቷን ገልጻለች።

"የመጀመሪያ ልጄን የምወልድበት ቀንና የምርጫው ቀን መገጣጠሙ ለእኔ ታሪካዊ ነው" ብላለች።

ልክ እኔ ልጄን ወልጄ እንደምገላገለው ኢትዮጵያም ካለችበት ችግር ተገላግላ ሠላም እንድትሆን ነው ምኞቴ  ብላለች።

የሲትራ መሐመድ ባለቤት አቶ ሳሚ ሚሊዮን እርግዝናዋን የሚከታተለው ዶክተር ሚስቱ ዛሬ እንደምትወልድ እንደነገራቸው ገልጿል።

ይሁንና እርሱና ባለቤቴ ወደ ሆስፒታል ከመሄዳቸው በፊት ድምፅ መስጠት አለብን በማለት በምርጫ ጣቢያው መገኘታቸውን ተናግሯል።

ባለቤቱ ቅድሚያ ወደ ምርጫ ጣቢያው የመጣችው በምርጫው የተሳተፉ ሴቶችን ለማበረታታት መሆኑንም ነው የገለጸው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ችግር ትሻገራለች ያለው አቶ ሳሚ፤ የሚመጡት ተመራጮችም ሠላምን ዋነኛ ትኩረት አድርገው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

በአዲስ አበባ ለሐረሪ ክልል ተወላጆች በተዘጋጁ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች ከአምስት ሺህ በላይ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም