በሶማሌ ክልል ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞ መምረጣቸው ልዩ ደስታ ፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞ መምረጣቸው ልዩ ደስታ ፈጥሮልናል
ጅግጅጋ ፤ መስከረም 2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞ በምርጫ መሳተፍ በመቻላቸው ልዩ ደስታና አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው በጅግጅጋ የሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆች ተናገሩ።
በጂግጂጋ ከተማ ለሚኖሩና በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ 1ሺህ 412 የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የጅጉል ልዩ የምርጫ ጣቢያ ተዘጋጅቶላቸው መርጠዋል።
ተወላጆቹም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ከማለዳው ጀምሮ በምርጫ ጣቢያው ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምፃቸውን ሲሰጡ ውለዋል።
መራጮቹ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚመርጡት ፓርቲ መንግሥት ሲመሰርት የሀገሪቱን አንድነትና ልማት ከማስጠበቅ ባሻገር የወጣቶችና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል ።
በጅግጅጋ ከተማ ለ40 ዓመታት እንደኖሩ የተናገሩት አቶ በረኸት ዓሊ "ዴሞክራሲያዊ መብቴ እንዲከበር ተደርጎ በምርጫው መሳተፌና የምፈልገውን በመምረጤ ተደስቻለሁ" ብለዋል።
''የዘንድሮ ምርጫ በሰላማዊነቱ፣በነፃነቱና በአካታችነቱ ከሌላው ጊዜ ምርጫዎች ተወዳዳሪ የለውም፤ ማንም ያሸንፍ ማን ውጤቱን በፀጋ ተቀብሎ ለተሻለ ልማትና ዴሞክራሲ ተባብሮ መስራት ይገባል'' ሲሉም ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሣፊያ ኢድሪስ በበኩላቸው ድምጻቸውን ለመስጠት በተመቻቸላቸው ዕድል በመጠቀም የፈለጉትን ፤መምረጥ በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ለመምረጥ የተነሳሱት በምርጫው የሴቶችን ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት እንዲጨምር፣ በሀገሪቱ ልማትና ዴሞክራሲ ለማሳፈን ባላቸው ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል።
ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገትና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ይሰራል ያሉትን ፓርቲ መምረጣቸውን የገለጹት፤ ደግሞ አቶ ሣላህ አደም ናቸው።
የመረጡት ፓርቲ መንግሥት ሲሆን የዜጎችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ ይሰጣል ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል።
ለሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የተመቻቸው ምርጫ ህገ መንግስታዊ የመምረጥ መብታቸውን በትክክል ያጎናፀፈ ነው ያለው ደግሞ ወጣት ሲራክ ጥበቡ ነው።
በህዝብ አመኔታ ተሰጥቶት መንግሥት የሚመሰረተው ፓርቲ የሀገሪቱንም ሆነ የሐረሪ ክልል ወጣቶችን ሥራ አጥነት ችግር እንደሚፈታ እምነቱ መሆኑን ገልጿል።
በጅግጅጋ በተቋቋመው የጅጉል ልዩ ምርጫ ጣቢያ ብልፅግና ፓርቲና የሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ለክልልና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ለውድድር ቀርበዋል።
በሐረሪ ክልል ዛሬ በተካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልፅግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፣አዲስ ትውልድ ፓርቲ ፣እናት ፓርቲ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ለውድድር መቅረባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።