ቀጥታ፡

የእሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር መሥራት አለብን - የአባ ገዳዎች ኅብረት

መቱ፤ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) ኢሬቻ የምስጋናና የዕርቅ የወንድማማችነትም በዓል እንደመሆኑ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ትኩረት ሰጥተን መሥራት አለብን ሲሉ የኢሉባቦር ዞን አባ ገዳዎች ኅብረት ገለፀ።

ኅብረቱ በዞኑ  የእሬቻ በዓልን ለማክበር ወደ ሥፍራው ከሚጓዙ አካላት መደረግ ባለባቸው ጥንቃቄዎችና ኃላፊነቶች ዙሪያ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቱ ከተማ ውይይት ተካሄዷል።

ከኅብረቱ አመራሮች መካከል አባ ገዳ ተሰማ ሙሉነህ  እንደተናገሩት፤ በመጪው መስከረም 23/2014ዓ.ም. በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ለመታደም ከዞኑ የሚንቀሳቀሱ አካላት የአካባቢውን የሰላም አምባሳደርነት በሚያጎላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሆን አለበት።

በዓሉ የኃይማኖት፣ የጀግንነት ወይም የውድድርና የፖለቲካ አጀንዳዎች ማራመጃ መድረክ ባለመሆኑ ማንኛውም ተሳታፊ አካል እራሱንም ሆነ አካባቢውን በዚህ አውድ በመቃኘት ለሰላማዊነቱ የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል።

አባ ገዳ ኃይሉ ለገሰ በበኩላቸው፤  በዓሉን ለማክበር በምናደርገው ጉዞና በበዓሉ ስፍራ እንቅስቃሴዎቻችን የሰላማችን ጠባቂዎችም እኛው መሆናችንን በደንብ መገንዘብ ይኖርብናል ነው ያሉት።

በዓሉ ሰላማዊ እንዳይሆን የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ መገንዘብና አካባቢያችንን በንቃት መከታተል ይኖርብናል ያሉት አባ ገዳ ኃይሉ፤ በዚህም መስከረም 24/2014ዓ.ም ለሚደረገው የመንግስት ምስረታም ሀገር ሰላም እንድትሆን ፈጣሪን መለመንና የድርሻችንንም መወጣት አለብን ብለዋል።

ወጣት ከሊፋ ረጋሳ፤ የኢሬቻ በዓል ሰላማዊና ወንድማማችነት የተረጋገጠበት የመተባበር በዓል መሆኑን ለማጉላት ከዝግጅቱ ጀምሮ ሁሉም አካላት የየድርሻችንን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅብናል ሲል ተናግሯል።

በውይይትመድረኩ  የተገኙት የኢሉባቦር ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ሰለሞን ታምሩ ባስተላለፉት መልዕክት  የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል  እንደሀገር ትላልቅ ድሎችን ባስመዘገብንበት ማግስት የምናከብረው ነው ብለዋል።

በዓሉ  የሰላም፣የወንድማማችነትና አንድነት መሆኑን ለዓለም የምናስተዋውቅበት ሌላኛው ዕድላችን በመሆኑ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

ከበዓሉ ዓላማ ውጪ ያሉ ማናቸውም የጀግንነት፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካና የውድድር ዓላማዎችን የሚያንፀባርቁ አልባሳት፣ መፈክሮችና የመሳሰሉትን ማድረግ እንደማይገባ ታውቆ ዝግጅቱም በዚህ አግባብ መታሰብ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ የበዓሉ ሰላም ጠባቂና ባለቤት መሆኑን መገንዘብ ይገባዋል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች፣ ቄሮዎችና የዞኑ  አመራሮች ተገኝተዋል።

የዘንድሮ እሬቻ በዓል  መስከረም 22 በአዲስ አበባ/ሆራ ፊንፊኔ/ ፣  በማግስቱ ደግሞ  በቢሾፍቱ /ሆራ አርሰዲ /ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም