ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተወሰኑ ሥራዎችን ለሦስተኛ ወገን አስተላለፈ

አዲስ አበባ ነሃሴ 10/2010 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተወሰኑ ሥራዎችን በሦስተኛ ወገን በማሰራት አገልግሎቱን ለማሻሻል ማቀዱን ገለጸ። የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ማዕከላት ግንባታ፣ በጥገናና በኦፕሬሽን ዘርፎች የተመረጡ ሥራዎች በሦስተኛ ወገን የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው። የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ እንደገለጹት ከደንበኞች በተደጋጋሚ የሚቀርቡ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችን ለመፍታት በኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ማዕከላት ግንባታ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ይሳተፋሉ። ለሦስተኛ ወገን የሚተላለፉት ሥራዎች በኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፋፊያ ማዕከላት ግንባታ፣ በጥገናና ኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ የሚታዩ የጥራትና አገልግሎት ችግሮችን ይፈታሉ ብለዋል። የተቋሙ ሥራዎች ሦስተኛ ወገን እንዲሳተፉ መደረጉ መንግስት ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል እንደሆነ የገለጹት አቶ ብዙወርቅ የግሉን ዘርፍ በኤሌክትሪክ ኃይል ሥራዎች ላይ ለማሰማራት የተያዘ አቅጣጫ እንደሆነ ተናግረዋል። የተቋሙን ደንበኞች በቅርበት ለማገልገል በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ያልተማከለ የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት 490 ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። ከአገልግሎት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት ያልቻለው ተቋሙ የሚጠቀመው ቴክኖሎጂ ኋላቀር በመሆኑ ነው በማለትም ለቅሬታዎቹ መፍትሄ ለመስጠት በኔትወርክ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ማዕከላትና በኦፕሬሽን ሥራዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ተቋሙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን የታሪፍ ማሻሻያው እስከ 100 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ሰዎችን እንደማያካትት ተናግረዋል። ለመንግስት የቀረበው ረቂቅ ሰነድ ሲጸድቅ ዝርዝር መረጃ ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም