ቀጥታ፡

የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሃይማኖት ተቋማት የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ ተጀመረ

መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምን ዓላማ ያደረገና ሁሉም የሃይማኖት ተቋማትና ምዕመናን የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሲሆን የቴክኒክ ጉዳዮችን ሠላም ሚኒስቴር እንደሚያከናውን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የሃይማኖት አባቶችና በሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጉባዔው ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች መከሰታቸውን አስታውሰዋል።

በተለይም በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የነበሩ የህልውና ዘመቻ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋና የጎርፍ መጥለቅለቅ ከተፈጠሩ ፈታኝ ክስተቶች መካከል ጠቅሰዋል።

በዚህ ሳቢያም ዜጎች በርካታ ችግሮችና ፈተናዎችን እየተጋፈጡ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ መላው ሕዝብ ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለይ በአስቸጋሪው ወቅት ከወገኑ ጎን መሆኑን በተለያዩ ድጋፎች እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸው ይህ የሚበረታታና ሊቀጥል የሚገባ ነው ብለዋል።

ቀሲስ ታጋይ የሃይማኖት ተቋማትና ምዕመናንም በራሳቸው ተነሳሽነት ወገኖቻቸውን በገንዘብና በአይነት ሲደግፉና ሲያግዙ እንደቆዩም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ይህን መልካም ተግባር በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ሁሉም ሃይማኖቶች መተዛዘንና መረዳዳትን የሚያስተምሩ በመሆኑ የጋራ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ማካሄድ አስፈልጓል ብለዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያው የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት በራሳቸውና በምእመኖቻቸው ስም ድጋፍ የሚያደርጉበት እንደሆነም አብራርተዋል።

ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማትና ምእመናን የሚሰበሰበው ገንዘብ በአንድ ቋት እንዲጠራቀም ለማድረግም የባንክ ሂሳብ ተከፍቶለታል ብለዋል።

ሂደቱን በታማኝነት በማስተባበር ረገድ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጀምሮ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አጽንኦት ሰጥተው እንዲሰሩም አሳስበዋል።

በመግለጫው ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶችም መተዛዘንን፣ መረዳዳትንና በክፉ ጊዜ መደራረስን የሁሉም የእምነት ተቋም አስተምህሮ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን መርዳትና ማቋቋም የሁሉም አማኞች ግዴታ መሆኑን በመጠቆም ከመርዳት ባለፈ ፈጣሪ የሚደሰትበትና የሚባርክበት እድል መሆኑን አንስተዋል።

ምዕመኑ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ በበጎ ተግባር ላይ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም የሃይማኖት አባቶቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው አገሪቷ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን እያሳለፈች ነው ብለዋል።

ችግሩን በመገንዘብ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተጎዱ ወገኖች ከሚያደርጉት ድጋፍና ትብብር ባሻገር የሃይማኖት አባቶች አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ በአንድ መንፈስ ፈጣሪውን የሚለምንበት የምህላና የጸሎት መርሃ ግብር እንዲኖር በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን መወጣታቸውን አስታውሰዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ኑሯቸውን በፈተና እየመሩ ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ተቋማቱ ምዕመኑን በማስተባበር በራሳቸው ተነሳሽነት የገቢ ማሰባሰቢያ ማዘጋጀታቸው የሚያስመሰግን ተግባር ነው ብለዋል።

የሠላም ሚኒስቴር ዘመቻው ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ብሔራዊ የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዲወጣና ተግባራዊ እንዲደረግ በማድረግ ሃላፊነቱን ተወጥቷል፤ ድጋፉንም ያጠናክራል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የሠብዓዊ ድጋፉን በሚመለከት ከጉባኤውና ከሠላም ሚኒስቴር የተውጣጡ አባላት ያሉት ብሔራዊ  አቢይ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ "የላቀ በጎነትና ሠብዓዊነት ለአገራችን ሠላም" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወን ይሆናል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተከፈተው የባንክ ሒሳብ አገራዊ የሠብዓዊ ድጋፍ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ለአገር ውስጥ ገንዘብ 1000430591251 የባንክ ሂሳብ ማበርከት ይቻላል።

በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ድጋፉን መቀላቀል ለሚሹ አካላትም Ministry of peace Ethiopian religious institutions relief fund በሚል ማንኛውንም የውጭ አገር ገንዘብ ማስገቢያ ቁጥር 010001300080 ገቢ ማድረግ ይቻላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም