ቀጥታ፡

ተቋማቱ አገራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም ጉዳዮችን ለማሳካት በጋራ ይሰራሉ

መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በአገራዊ መግባባትና በእርቀ-ሰላም ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ተልዕኳቸውን ውጤታማ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።
አዲስ መንግሥት መመስረቻ ዋዜማ ላይ የተደረገው ስምምነት ከተቋም በላይ የአገር ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎችን ለማከናወን ዕድል እንደሚሰጥም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤና የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለ ኃይሉ ናቸው።

የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሁለቱ ተቋማት ተመሳሳይ የሆነ አገራዊ ዓላማን ለማሳካት የሚሰሩ ናቸው።

በህዝቦች መካከል ስምምነትን፣ እርቅንና መከባበርን ለመፍጠር እንዲሁም የአገሪቷን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራታቸው ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ኢዜአ በመላ አገሪቷ ተደራሽ እንደመሆኑ የኮሚሽኑ ሥራዎች በህዝብ ዘንድ ለማሳወቅ፣ የሰላምና የእርቅ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎች በስፋት ለማሰራጨት ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሁለቱ ተቋማት በጋራ መሥራታቸው የተሰጣቸውን አገራዊ ተልዕኮ በውጤታማነት ለመፈጸም ያስችላቸዋል።

ኮሚሽኑ አገራቸውን በእውቀትና ሙያቸው ያገለገሉ አንጋፋ የአገር ባለውለታዎችን መያዙን ጠቁመው፤ "ኢዜአ በአገራዊ መግባባትና በእርቀ-ሰላም ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ሥራ መስራት ያስችለዋል" ብለዋል።

ኮሚሽኑ ዜጎች የሚያነሷቸው የዘመናት ቅራኔዎችና ቁርሾዎች ለመመለስ አገራዊ ለውጡ የወለደው ተቋም መሆኑንም አቶ ሰይፈ ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት በመመስረቻ ዋዜማ የተደረገው ስምምነት "ከተቋም በላይ የአገር ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎችን ለማከናወን ዕድል ይሰጣል" ነው ያሉት።

የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን  በኢትዮጵያ  ለበርካታ ዓመታት  በተለያዩ  ማህበረሰባዊና  ፖለቲካዊ  ግጭቶች  ምክንያት  በህዝቦች  መካከል የተደራረቡ  የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ለማውረድ ታህሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም