ኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት አዎንታዊ ምላሽ አግኝታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት አዎንታዊ ምላሽ አግኝታለች
መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፎ ላይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት አዎንታዊ ምላሽ አግኝታለች።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የልኡካን ቡድን የኒው ዮርክ ቆይታ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን በተመለከተ ለአገራትና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች በማስረዳት አዎንታዊ ምላሽ ማገኘቱ ተገለጿል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የልዑካን ቡድን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 76ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተደረገውን ተሳትፎ አብራርተዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጉዳይ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ካላቸው ፋይዳ አኳያ ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል።
ከኖርዌይ፣ ዴንማርክ ፣ ህንድ ፣ ጋቦን ፣ አረብ ኢምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር ውይይት ካደረጉት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ነባራዊ ሁኔታ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ኢትዮ-ሱዳን ድንበርና ሌሎች ዋና ዋና አጀንዳዎችን በሚመለከትም አቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሸባሪው ቡድን በአፋር፣ ማይካድራና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የፈጸመውን ተግባር ማውገዝ ያልቻሉበት ሁኔታ ላይ በውይይቱ ላይ በግልጽ ንግግር ከተደረገባቸው መስኮች መሆናቸውን ጨምረዋል።
ከአገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የተደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ነጻነትና አንድነት መነካት እንዳሌለበት አንስተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት /ተመድ/ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎችም በኢትዮጵን ወቅታዊ ሁኔታና የሰብዓዊ እርዳታ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አሁን ያለበት ደረጃ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በኢትዮጵያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በአሸባሪው ህወሃት ምክንያት በአማራና አፋር ክልሎች በመኖራቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እንዲገነዘቡ በአጽንኦት ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የዓለም የምግብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶችም በአፋርና አማራ ክልሎች ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል።
ከሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ ተኩስ በማቆም ንግግር መደረግ እንዳለበት ላነሱት ጥያቄም በተሰጠው ምላሽ መንግስት የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ በመጣስ አሸባሪው ህወሃት እያደረሰ ያለው ጉዳት ተብራርቶላቸዋል።
"የድርድሩም ሆነ ሰላማዊ መፍትሄው መጨረሻ የሚቋጨው አሁን የሚመሰረተው አዲስ መንግስት በሚያወጣው ፍኖተ ካረታ (Roadmap) ነው" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ጨምረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የሚጀመርበትን ቀን በተመለከተም ኢትዮጵያ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፤ ግብጽና ሱዳን ድርድሩን ከአፍሪካ ህብረት ለማውጣት የሄዱበት በንገድ እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል።
እንደ አምባሳደር ዲና መግለጫ ''የነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተመንግስት'' ንቅናቄን ጨምሮ በተለያዩ የመረጃ አማራጮች "የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ናቸው" ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስትን የችግሩ ተጠያቂ አድርጎ ለማንሳት የሚሰሩ ነገሮችን እንዲቀንሱ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የህዝብ ድጋፍ እንደሌለው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ብቻውን እየገነባ እንደሆነ ተደርጎ የተሰራጨው የተሳሳተ መረጃን አስመልክቶም "የነበረው አሉታዊ አረዳድ እንዲቀየር እያደረገ ነው" ብለዋል።
"መንግስት ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ንግግር ጀምሯል" በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ አሁን ላይ የተጀመረ ምንም አይነት ነገር አለመኖሩን አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለሱ ሂደት የቀጠለ ሲሆን፤ ባለፉት ሳምንታት ከሪያድ 794፣ ከጅዳ 892፣ ከየመን 357 ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።