የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሴቶች፣ ወጣቶችና ከስደት ተመላሾች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ከስደት ተመላሾችና ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ለመንግስት ተቋማትና ለአጋር አካላት ይፋ አድርጋለች።
 ፕሮጀክቱ በተለይ ስራ አጥ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ከስደት ተመላሾችና በአዲስ አበባ የሚገኙ የሌሎች አገራት ስደተኞች የተለያየ ሙያ ስልጠና የሚሰጥበትና የስራ እድል የሚመቻችበት ነው ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ በሚካሄደው የመጀመሪያ ምዕራፍ የፕሮጀክቱ ትግበራ ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ በመዲናዋ የሚገኙ የኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳንና የየመን ስደተኞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው የተገለጸው።  

የቤተክርስቲያኗ የአዲስ አበባ ሰበካ ሃዋሪያዊ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አባ ጴጥሮስ መርጋ ለኤዜአ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚተገበርና በሚያስገኘው ውጤትም እንደሚራዘም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን በቤተክሪስቲያኗ ስር ከሚገኙ አራት የልማት ተቋማትጋር በመጣመር መቀረፁንና ስልጠና ከመፍጠር ጀምሮ የስራ እድል ማመቻቸትና ክትትል የማድረግ ሀላፊነቶችን ተከፋፍለዋል ብለዋል።

ከስደት የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ከሚደርስባቸው የስነ ልቦና ጫና እንዲያገግሙ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የስነ ልቦና ድጋፍ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ለሚታቀፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል በመፍጠሩ ሂደት መንግስትን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በራሳቸው አቅም የራሳቸውን ስራ ለሚፈጥሩም በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል።

ፕሮጀክቱ ሰፊና የተለያዩ ይዘቶች ያሉት በመሆኑ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም አመልክተዋል።

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እዮብ አወቀ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ ማኅበራዊ ሃላፊነቷን ለመወጣት የምታከናውነው ተግባር በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ከስደት ተመላሾችና የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው ፕሮጀክቱ ስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።

ኤጀንሲ በሚያስፈልገው ሁሉ ፕሮክቱን ለማገዝ ያለውን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።

እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚው ውስጥ ተሳትፈው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ በተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚከወን ባለመሆኑ የእርዳታ ሰጪዎችና የመንግስት ተቋማትን የጋራ ትብብር ይፈልጋልም ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ቀጣይ ምዕራፍ በሶማሌ፣ በትግራይ፣ በአማራና በጋምቤላ ክልሎች እንደሚተገበር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም