ቀጥታ፡

በሐረሪ፣በሶማሌና በደቡብ ክልሎች አገራዊ ምርጫዎች የጸጥታ ችግር አላጋጠመንም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) በሐረሪ፣በሶማሌና በደቡብ ክልሎች ዛሬ እየተካሔደ ያለው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ሠላማዊ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገለፁ።

ሰብሳቢዋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሐረሪ፣ ሶማሌና በደቡብ ክልሎች እና በድሬዳዋ አንድ ምርጫ ጣቢያዎች ከማለዳው ጀምሮ ሠላማዊ የድምጽ መስጠት ሂደት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

እስካሁን በየምርጫ ጣቢያው በተደረገ ሪፖርት ያጋጠሙ የቁሳቁስ ጉድለት ጥቃቅን ችግሮችን በመከታተልና በመፍታት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በተገቢው መንገድ እንዲቀጥል መደረጉን ጠቅሰዋል።

በአካባቢዎቹ ሁሉም የጸጥታ አካላት እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀው፤ይህ ነው የሚባል የጎላ የፀጥታ ችግር አለመድረሱን ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ሞያሌ ምርጫ ክልል አስፈፃሚዎች የፀጥታ ስጋት ገጥሞናል በማለታቸው ምርጫው እንዲቆም መደረጉንም ገልፀዋል።

በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ምርጫ ክልል ደግሞ ቀደም ብሎ በፀጥታ ችግር ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ ባይከናወንም መራጮች በዛሬው እለት እየተመዘገቡ ድምፃቸውን እየሰጡ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በዚሁ ምርጫ ክልል ከመደበኛው ምርጫ ባሻገር የሕዝበ ውሳኔ ድምጽ የሚሰጥበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰብሳቢዋ የተፎካካሪ ዕጩ ወኪሎችም በሠላም የድምፅ አሰጣጡን ሂደት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዳውሮ ዞን ለእስር የተዳረገ አንድ የምርጫ ታዛቢ እስራቱ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲፈታ ተደርጎ መታዘቡን መቀጠሉንም ተናግረዋል።

ይህን ያደረጉ አካላትን አጣርተን ተጠያቂ እንዲሆኑ እናደርጋለንም ብለዋል።

ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ የምርጫ ቁሳቁስና ሰነዶች አያያዝና አከፋፈት፤ ጊዜና ሁኔታ በተመለከተ ለአስፈጸሚዎች ተገቢው ስልጠና ስለመሰጠቱም አስታውሰዋል።

በሶስቱ ክልሎች በሚካሄደው ምርጫ 22 የፖለቲካ ድርጅቶች እና 106 የግል ዕጩዎች እንደሚወዳደሩ ተገልጿል።

እንዲሁም 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን መራጮች በ7 ሺህ 54 የምርጫ ጣቢያዎች ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም