አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ደባ እየፈጸመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ደባ እየፈጸመ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ "በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ደባ እየፈጸመ ነው" ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ገለጸ።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለውስጥ በስውር እጃቸው የኢትዮጵያ ሕዝብን ሲያውኩ የቆዩት አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ሕብረታቸውን ይፋ ካደረጉ ሰንብተዋል።
አሸባሪው ሕወሓት የመንግሥት ሥልጣን በተቆጣጠረበት ዘመን የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በአሸባሪነት ማስፈረጁ ይታወሳል።
አሁን የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት ሲል "ሸኔ" ከተባለ አሸባሪ ቡድን ጋር በሕብረት እንደሚሰራ በይፋ ገልጿል።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ኢዜአ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀ መንበር ከአቶ ቀጄላ መርዳሳ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አቶ ቀጄላ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር "በመንግሥት የቀረበለትን የሰላማዊ ትግል ጥሪ ተቀብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል" ብለዋል።
ኦነግ ለረጅም ዓመታት ካደረገው የትጥቅ ትግል ይልቅ የኦሮሞ ወጣቶች ባካሄዱት ሰላማዊ ትግል ያመጣውን ለውጥ ማንሳት ይቻላል በማለትም የሰላማዊ ትግል አስፈላጊነትን ያነሳሉ።
እንደ አቶ ቀጄላ ገለጻ፤ ከሰላማዊ ትግል ውጭ ለኢትዮጵያ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፋይዳ የለውም።
በዚህ ወቅት በትጥቅ የታገዘ ትግል ማድረግ የአገሪቷ ሉዓላዊነት እንዲደፈር በር መክፈት መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
"ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ያበረው አሸባሪው ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታሪካዊ ደባ እየፈጸመ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል" ብለዋል ምክትል ሊቀ መንበሩ።
አሸባሪው ሕወሓት የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ሁሉ በደል መረሳቱ የሚያሳዝን መሆኑን አመልክተው፤ አሸባሪው ሸኔ ዛሬ በእንዲህ ዓይነት መልኩ መምጣቱ እጅግ የሚያሳዝን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ጥምረቱም አሸባሪው ሕወሓት እንደለመደው የኦሮሞን ሕዝብ "እርስ በርሱ እንዳይግባባ በማድረግ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት ነው" ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት አሸባሪው ሸኔ በሚያደርገው የሽብር እንቅስቃሴ የኦሮሞን ሕዝብ ስቃዩን እያየ መሆኑን አቶ ቀጄላ ተናግረዋል።
በመሆኑም የኦሮሞ ሕዝብ ለአሸባሪው ሕወሓት እንዳልተንበረከከው ሁሉ "ለአሸባሪው ሸኔ አይንበረከክም" ብለዋል።
ሕዝቡ ፊት ለፊት ወጥቶ አሸባሪውን ሸኔ እንዲቃወምና እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።