በፀሃይ ብርሃን የሚሰሩ መገልገያዎችን ተስማሚነትና ጥራት ለመቆጣጠር ስምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በፀሃይ ብርሃን የሚሰሩ መገልገያዎችን ተስማሚነትና ጥራት ለመቆጣጠር ስምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ መስከረም 20/2014 የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት በፀሃይ ብርሃን የሚሰሩ መገልገያዎችን ተስማሚነትና ጥራት ለመቆጣጠር ከሁለት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት አድርገዋል።
ስምምነቱ ኮቴክ እና ቢሮቬርታዝ ከተሰኙ ሁለት የተስማሚነትና የጥራት ደረጃዎችን ከሚያወጡ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር ነው የተደረገው፡፡
ዓላማውም ማንኛውም በጸሀይ ብርሃን የሚሰራ መገልገያ ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ጥራቱ ተፈትሾ እንዲገባ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አስመጪዎች ይህን አሳውቀው ሲሰሩ እንዳልነበረ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ሳቢያም በፀሃይ ብርሃን የሚሰሩ ቁሶችን በስፋት የሚጠቀመው የገጠሩ ኅብረተሰብ በጥራት መጓደል ላልተገባ ወጪ ሲዳረግ መቆየቱ ተመላክቷል።
ስምምነቱ እቃዎቹ ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው አስቀድሞ ከሚጫኑበት ቦታ ተገቢውን የጥራት ደረጃ ማሟላታቸው ተፈትሾ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሀና እንዳሉት ስምምነቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ በጸሀይ ብርሃን የሚሰሩ መገልገያዎች አስተማማኝ ጥራት እንዲኖራቸው ይረዳል።
ከአጠቃላዩ ሕዝብ 35 በመቶ የሚሆነው በአማራጭ የኃይል አቅርቦቶች ተጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው ስምምነቱ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች የሚያደርሱትን ኪሳራም ይቀንሳል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ማናቸውም በፀሀይ ብርሃን የሚሰሩ መገልገያዎች ከ350 ዋት በላይ የማመንጨት አቅም እንዲኖራቸው ደረጃ ወጥቶላቸዋል ብለዋል።
ስምምነቱ ኩባንያዎቹ ምርቶቹ ከሚጫኑበት ቦታ ያላቸውን ጥራት በመፈተሽ አስፈላጊውን የጥራት ደረጃ ማሟላታቸውን ለማረጋገጥ የተደረገ መሆኑን አክለዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት ኩባንያዎች ተወካዮች በዘርፉ ዓለምአቀፍ ልምድ እንዳላቸው በመግለጽ ስራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።