አሲዳማ አፈርን ለማከም ለአርሶ አደሮች ኖራ በግዥና በብድር የሚያገኙበት ሥርዓት ተዘርግቷል - ኢዜአ አማርኛ
አሲዳማ አፈርን ለማከም ለአርሶ አደሮች ኖራ በግዥና በብድር የሚያገኙበት ሥርዓት ተዘርግቷል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) አሲዳማ አፈርን ለማከም ለአርሶ አደሮች ኖራ በግዥና በብድር የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር የአፈርን ለምነት በሚያሻሽሉ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ አገሪቷ በአፈር ለምነት ዙሪያ እያከናወነች ያለውን ተግባር፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር ተፈራ ሰለሞን እንደተናገሩት፤ አፈር ለግብርና ሥራ መሰረት ቢሆንም በመንከባከብ ረገድ ሰፊ ክፍተቶች የሚስተዋልበት ነው።
በተለይም እውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ የአፈርን ለምነት መጠበቅ ላይ ያሉ ችግሮች ብዙ መሆናቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራት በፖሊሲ ሊታገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ ተፈራ እንደሚሉት፤ የአፈር ለምነት በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች እየተሟጠጠ ነው። በተለይም የሰሜኑ ክፍል ወደ ኮረትነት እየተቀየረ ነው።
"ይህ ደግሞ ምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሜካናይዝድ እርሻ እንዲሁም የመስኖ እርሻዎችን ለማከናወን የአፈር እንክብካቤ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
አርባ ሦሰት በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ ክፍል በእንክብካቤ ጉድለት ሳቢያ ወደ አሲዳማነት እየተቀየረ መሆኑን አመልክተው፤ አርሶ አደሩም የአፈርን ለምነት መጠበቅ ላይ በቂ ግንዛቤ አለው ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል።
የእርሻ መሬት አያያዝና እንክብካቤ የህግ ማዕቀፍ መኖር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ያስረዳሉ።
"ወተት የምትሰጥ ላም ካልተንከባከብናት ወተት ልትሰጥ አትችልም፤ አፈርም እንደዚሁ ነው።" ሲሉ ያስረዱት።
አገሪቷ ካላት የሚታረስ 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ አሲዳማ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚሁ ውስጥ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታሩ ህክምና ካላገኘ ምርት መስጠት የማይችልበት ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
የግብርና ሚኒስቴር አሲዳማ መሬትን በኖራ የማከም እንቅስቃሴን ባለፉት አስር ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን ያስረዳሉ።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም ሌላው ውጤት እየተገኘበት ያለ እንቅስቃሴ መሆኑን አመልክተዋል።
ለአርሶ አደሩ በተፈጠረው ግንዛቤ መሰረት የኖራ ፍላጎቱ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ሳቢያ አሁን ባሉት የኖራ አምራች ፋብሪካዎች የአርሶ አደሩን የኖራ ፍላጎት ማሟላት እንደማይቻል ጠቅሰዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት የግል አምራቾች ለአርሶ አደሩ "ልክ እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በግዥ ወይም በብድር እንዲቀርብለት የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል" ብለዋል።
በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች ላይ የኖራ አምራቾችና ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንደተለዩም አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት ጊዜያት ኖራን ለአርሶ አደሩ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማቅረብ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ምርትን ከማምረት ውጭ የነበሩ መሬቶች በተደረገው የኖራ ህክምና ማምረት እንዲችሉ መደረጉን አቶ ተፈራ ገልጸዋል።
ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ወደ ምርታማነት መመለሱን አብራርተዋል።
የፔለም ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ኃይሉ አርአያ በበኩላቸው፤ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ አንዱ ዘዴ ማዳበሪያ በትክክል ለሚፈለገው እጽዋት እንዲደርስ ማድረግ መሆኑን ያነሳሉ።
ከዚህ ባለፈም በአንድ የእርሻ ቦታ ላይ የተለያዩ ሰብሎችን መዝራት፣ አፈር ውስጥ ህይወት ያላቸው ነገሮች እንዲኖሩ ማድረግና የአፈሩን እርጥበታማነት ማዝለቅ ውጤታማ ከሚያደርጉ ሥራዎች መካከል እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ተመክሯቸውን ካጋሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሲሳይ ተፈራ እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በመጠቀማቸውና የግብርና ባለሙያ ምክሮችን በመተግበራቸው ውጤት ማግኘታቸውን አብራርተዋል።
"ከዚህ በፊት አፈሩን በአግባቡ ባለመንከባከቤ በቂ ምርት አላገኝም ነበር" ያሉት አርሶ አደሩ፤ አሁን ግን ጥሩ ምርት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።