በሶስቱም ክልሎች አገራዊ ምርጫዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት በሠላም እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶስቱም ክልሎች አገራዊ ምርጫዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት በሠላም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2014(ኢዜአ) በሐረሪ፣ በሶማሌና በደቡብ ክልሎች አገራዊ ምርጫዎች የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሠላም እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ገልጸዋል።
የምርጫ ቁሳቁስ አያያዝን በተመለከተ ታዛቢዎች ባሉበት ታይቶና ተፈትሾ ድምጽ መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል።
በሐረሪ ክልል በሚገኝ ምርጫ ጣቢያ የድምፅ መስጫ ሳጥን ተከፍቶ መገኘቱንም ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል ሞያሌ ምርጫ ክልል አስፈፃሚዎች የፀጥታ ስጋት ገጥሞናል በማለታቸው ምርጫው እንዲቆም መደረጉንም ገልፀዋል።
በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ምርጫ ክልል ደግሞ ቀደም ብሎ በፀጥታ ችግር ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ ባይከናወንም መራጮች በዛሬ እየተመዘገቡ ድምፃቸውን እየሰጡ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚሁ ምርጫ ክልል ከመደበኛው ምርጫ ባሻገር የሕዝበ ውሳኔ ምርጫም የሚካሄድበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዳውሮ ዞን ለእስር የተዳረገ አንድ ምርጫ አስፈፃሚ እስራቱ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲለቀቅ መደረጉንም አንስተዋል።
በሶስቱ ክልሎች በሚካሄደው ምርጫ 22 የፖለቲካ ድርጅቶች እና 106 የግል ዕጩዎች እንደሚወዳደሩ ተገልጿል።
እንዲሁም 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን መራጮች በ7 ሺህ 54 የምርጫ ጣቢያዎች ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
ጥቃቅን ችግሮችን በመከታተልና በመፍታት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እየቀጠለ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ።