በተባበሩት መንግስታት ጉባዔ የተሳተፈው ልዑክ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት ውጤታማ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በተባበሩት መንግስታት ጉባዔ የተሳተፈው ልዑክ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት ውጤታማ ሆኗል
አዲስ አበባ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ የተሳተፈው ልዑክ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት ረገድ ውጤታማ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ያለፉትን ሁለት ሣምንታት የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብትና ዜጋ ተኮር ዲፖሎማሲ ተግባራት ክንውንን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በተባበሩት መንግስታት 76ኛ ጉባዔ ስለነበረው ተሳትፎ አስረድተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል።
በሕዳሴ ግድብ፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሁኔታና ሌሎች ጉዳዮች ስላሉ ሁኔታዎች ማስረዳታቸውንም እንዲሁ።
የሠብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚያስፈልገው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአሸባሪው ህወሓት አማካኝነት በአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች እንደሆነም አስረድተዋል ነው ያሉት።
በመሆኑም ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ይህንኑ ተረድተው ድጋፍ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውንና ድርጅቶቹም አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
በውይይቶቹ ላይ የተሳተፉ መሪዎች 'የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት የማይነካ' ስለመሆኑ ማንሳታቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጉባዔው በኮቪድ-19፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአገራት ግንኙነትና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ በማተኮር ንግግር ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማስረዳት አገሪቷ የሚደረግባትን ጫና እንደማትቀበልም አብራርተዋል ብለዋል።