የአማራ ክልል ህዝብ ህልውና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ህዝብ ህልውና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው
ባህርዳር፤ መስከረም 20/2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ህዝብ ህልውና የሚረጋገጠው ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተሳሰረ የትግል አቅጣጫ በመከተል መሆኑን ተገንዝበው እንደሚሰሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ገለጹ።
ርዕሰ-መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ቀርበው ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ሃገርና የክልሉ ህዝብ በአሸባሪውና ወራሪው ህወሃት ጫና በተፈጠረበት ወቅት የተረከቡት ከባድ ሃላፊነት ያላቸውን አቅም ሁሉ በመጠቀም ጠንካራ ትግል እንዲያደርጉ ያነሳሳ ነው።
በአሸባሪው ህወሃት በተፈጸመበት ወረራ በአስከፊ መከራና ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ህዝብ ከዚህ ችግር ለመታደግ ከሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉን ልዩ ሃይሎች፣ ከፋኖና ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት የሚካሔደው ትግል ለውጤት እንደሚበቃም ተናግረዋል።
"አዲስ የተመሰረተው የክልሉ መንግስትም አሸባሪው የህወሃት ቡድንን በመደምሰስ ዜጎችን ነጻ ከማውጣት ባሻገር ቡድኑ ለሃገር ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ዋና ትኩረታችን ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኑን ዓላማና ፍላጎት በተጠናከረ ትግል በማምከን የህዝቡን የመልማትና የመበልጸግ ፍላጎትና ተስፋ ማሳካት እንደሚገባ የገለጹት ዶክተር ይልቃል ይህም በአገር ግንባታና የነበረ እሴቱን በማበልጸግ እንዲሳተፍ ይደረጋል ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ማካሄዱን ጠቁመው "ይህን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የአለም መንግስታትና ድርጅቶች ሊያወግዙት ይገባል" ብለዋል።
"መላው የአማራና የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና የሚረጋገጠው በአንድነት፣ በመተሰባሰብና በመረዳዳት የገጠመንን ፈተና በድል በመወጣት ነው" ያሉት ርዕሰ-መስትዳደሩ ትብብሩ በሁሉም በኩል ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
"አሁን ላይ አዲስ መንግስት ስንመሰረት ህዝባችንን ከተጋረጠበት ችግር በማውጣት ብልጽግናና ልማትን ለማጎናጸፍ ቁርጠኛ በመሆናችን ነው" ብለዋል።
80 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ የሚተዳደረበትን ግብርና በማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ዶክተር ይልቃል ተናግረዋል።
"በግብርናው ዘርፍ በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንት ትስስር፣ በመስኖ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ላይ በማተኮር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ይሰጣል" ብለዋል።
የክልሉን የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም፣ የስፖርት፣ ዘርፎችን በማጠናከር ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለሴቶች ተጠቃሚነት ለጤናና ለሌሎች የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ በንግግራቸው አመላክተዋል።
"አሁን ላይ ሃብታችንን፣ እውቀታችንንና ክህሎታችንን ሙሉ በሙሉ በህልውና ዘመቻው ላይ በማተኮር ህዝባችንን ነጻ ለማውጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረን የምንሰራበት ወቅት ነው" ብለዋል።
የቀድሞው ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርም ለዶክተር ይልቃል ከፍአለ የስልጣን ርክክብ በማድረግ መልክም የስራ ጊዜን ተመኝተውላቸዋል።