የአሸባሪው ህወሓትን ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን የምናመክንበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነን - አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ህወሓትን ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን የምናመክንበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነን - አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
መስከረም 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የአሸባሪው ህወሓትን የመስፋፋትና ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን የምናመክንበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነን" ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።
አፈ ጉባኤዋ እንደተናገሩት፤ ወረራውን ለመመከት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በገንዘብ፣ ልጆቹን በመላክና በቁሳቁስ እያደረገ ያለው ድጋፍ እየተመዘገበ ላለው ድል መሰረት ሆኗል።
አሁንም በአሸባሪው ቡድን ተወረው በሚገኙ የክልሉ አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎች በችግር ውስጥ እንዳሉ አመልክተዋል።
"እነዚህ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ እስኪወጡ ድረስ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ሃይሉና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የበለጠ ትግል የምናካሄድበት ምዕራፍ ላይ ነን" ብለዋል።
በቀጣይም አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ከክልሉ በማጽዳት ሙሉ በሙሉ ለመቅበር በአንድነትና በቁርጠኝነት በመሰለፍ ድል ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ አፈ-ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
"እየተካሄደ ባለው የህልውና ማስከበር ትግል የምክር ቤት አባላት የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ለመወጣት ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባናል" ሲሉም ተናግረዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው ተመልሰው በልማት ስራቸው እንዲሰማሩ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ህዝብና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ርብርብ እንዲያደርጉም ወይዘሮ ፋንቱ ጠይቀዋል።
"የምክር ቤት አባላትም በህግ የተሰጠንን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር የህልውና ዘመቻውን በድል ለመወጣት እንዲሁም የክልሉ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የብልጽግና ስራዎችን ለማፋጠን መስራት ይኖርብናል" ብለዋል።
አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት፤ የህዝብ አንድነት የሚሸረሽሩ ሃይሎችን በመመከት የተሟላ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ይሰጠዋል።
ምክር ቤቱ ባስቀመጣቸው አጀንዳዎች ተገቢነትና ትኩረት በሚሰጣቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ቀጥሏል።