ቀጥታ፡

ምርጫው ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ መሪዎችን ለመለየት ያስችለናል - የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች

መስከረም 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሶማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ በመሳተፍ አገርና ህዝብን የሚያገለግሉ መሪዎችን እንደሚመርጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት፤ ምርጫው ለህዝብ ዕድገትና እኩልነት የሚሰራ መንግሥት ለመመስረት ያስችላል።

በመሆኑም ነፃና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።

ምርጫ የአንድ አገር ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጫና በጉጉት የሚጠበቅ ክስተት መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ምርጫ ለዜጎች ሰላም፣ ልማትና እኩልነት የሚተጉ መሪዎችን ወደ ስልጣን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

''የምርጫ ካርድ የወሰድን ነዋሪዎች ድምፃችንን ማባከን የለብንም'' በማለትም መራጮች ካርዳቸውን እንዳያባክኑ መክረዋል።

የምርጫ ካርድን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ለአገር ሰላምና ዕድገት የሚሰሩ ዕጩዎች እንደሚመርጡም ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ምርጫው ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወሰነው መሠረት መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሶማሌና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫው እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም